ጉባዔው በ79 ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ 77ቱ ላይ ውሳኔ አሳለፈ
November 4, 2022
ለጋብቻ የሚደረግ ጥበቃ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት
December 21, 2022
Show all

“ከ 3 ሴቶች ውስጥ አንዷ ጾታዊ ጥቃት ይደርስባታል።”

ዓለም አቀፍ 16ቱ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ ቀናት ከህዳር 16 – ታህሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም  “ሴትን አከብራለሁ ጥቃቷንም እቃወማለሁ” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ኢትዮጵያ ለ17ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ ተከብሮ አልፏል።

በዓሉ በየአመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ16 ቀናት በተለያዩ ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል በሚዘጋጁ ንቅናቄዎች እንደሚከበር ይታወቃል።

በዓሉ የሚከበረው  በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከልና ለማስቆም በሚደረገው ርብርብ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ሚና እንዲጫወትና ድጋፉን እንዲያሳይ እንዲሁም በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን አስከፊ የመብት ጥሰት እንዲቃወም ለማነቃቃት መሆኑ ይነገራል።

እኤአ በ2021 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ጉዳይ መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ከ 3 ሴቶች ውስጥ አንዷ ጾታዊ ጥቃት ይደርስባታል:: እንዲሁም ከ 5 ሴቶች አንዷ 18 አመት ሳይሞላት ጋብቻ እንድትፈጽም ትገደዳለች::

በአሁኑ ሰዓትም በሀገራችን በሴቶች እና ህፃናት ላይ በርካታ አስከፊ ጥቃቶች እየተፈፀሙ እንደሚገኙ ይነገራል። በተለይም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ባሉት አለመረጋጋቶችና ግጭቶች የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች ሴቶች እና ሕፃናት ሲሆኑ አስገድዶ መደፈርን ጨምሮ የተለያዩ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች እንደሚፈፀሙ የተለያዩ አካላትና ተቋማት ሪፖርቶች ያሳያሉ።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 35 ተራ ቁጥር 4 ላይ በግልፅ እንደተደነገገው “ሴቶች ከጎጂ ባሕል ተፅዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን መንግሥት ማስከበር አለበት። ሴቶችን የሚጨቁኑ በአካላቸው ወይም በአዕምሯቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጎች፣ ወጎችና ልማዶች የተከለከሉ ናቸው” ሲል ይደነግጋል።

በዚህ አግባብ በሕገ መንግሥቱ በግልፅ በተደነገገው አስገዳጅ ድንጋጌ መሠረት መንግሥት ሴቶችን ከማንኛውም አይነት ጥቃት የመከላከልና ጥቃት ሲደርስም ጥቃት አድራሾችን በሚያስተምር መልኩ በመቅጣት አስተማሪ ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት።

ከዚህ ባሻገር ዋናውና ወሳኙ ጉዳይ ግን በዘንድሮው የነጭ ሪቫን ቀን(የፀረ_ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ) በነበረው “ሴትን አከብራለሁ ጥቃቷንም እቃወማለሁ” የሚለውን መሪ ቃል በመያዝ ሁሉም ሰው በተለይም ወንዶች የሴቶችን መብት ማክበርና ማስከበር እንዲሁም ጥቃት ፈፃሚዎችን ለሕግ በማቅረብና በመቃወም የሴቶችን ጥቃት መቀነስ ብሎም ማስቆም ይቻላል።