“ከ 3 ሴቶች ውስጥ አንዷ ጾታዊ ጥቃት ይደርስባታል።”
December 21, 2022
በሀይማኖታዊ ወይም በባህላዊ ተቋማት የመዳኘት መብት ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንጻር
December 28, 2022
Show all

ለጋብቻ የሚደረግ ጥበቃ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት

በአጀማ መለታ

ሀገራት ለጋብቻ የተለያየ ትርጉም የሚሰጡ በመሆኑ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አንድና ወጥ የሆነ ትርጉም የለውም፡፡ በአብዛኛዎቹ ሀገራት የሕግ ስርዓት ውስጥ ጋብቻ አንድ ወንድና ሴት በፍቃደኝነት በሕይወት ዘመናቸው አብረው ለመኖርና የየግላቸውንና የጋራ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሲባል የሚዋዋሉበት ስርዓት እንደሆነ ይስማሙበታል፡፡   

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34(1፣3) እና 13(2) መሰረት ሀገራችን በተቀበለቻቸው የአለምአቀፍ ስምምነቶች መሰረትም ፀንቶ ባለው ጋብቻ ውስጥ ባልና ሚስት እኩል መብት እንዳላቸው፣ይህም በጋብቻ ወቅት እኩል እንደሆኑ፤ በጋብቻ ጊዜም የተፈሩት ንብረቶች ላይ እኩል መብት እንዳላቸው እንዲሁም ጋብቻ ለቤተሰብ ተፈጥሮ መሰረታዊ መነሻ በመሆኑ በሕብረተሰቡና በመንግሥት ጥበቃ እንደሚደረግለት ጭምር ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 34 እና 35(2) ላይ እውቅና የሚሰጠው ለጋብቻ ብቻ እንጂ ለሌላ ግንኙነት እንዳልሆነ ከድንጋጌዎቹ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህም ባለፈ ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13(1) መሰረት በስራዎቻቸው ይህንን የተጣለባቸውን ግዴታ መወጣት እንዳለባቸው ተደንግጎ ይገኛል፡፡   

ይህ የሚያሳየው ጋብቻ የቤተሰብ የተፈጥሮ መነሻ በመሆኑ ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ፤ መንግሥትም ይህን ተቋም ጥበቃ ሊያደርግለት የሚችልበት የሕግ ማዕቀፍ የማዘጋጀት ግዴታ እንዳለበት ነው፡፡ በዚህም መሰረት ጋብቻ እንዴት ሊመሰረት እንደሚችል እና የተመሰረተው ጋብቻ እንዴት እና በምን ዓይነት ሁኔታ ሊፈርስ እንደሚችል የቤተሰብ ሕግ በማውጣት እንዲሁም በተመሰረተው ጋብቻ ውስጥ ተጋቢዎች ሊኖራቸው የሚችለውን መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና እንዲኖረው በማድረግ አረጋግጧል፡፡  ከጋብቻ አመሰራረት ጋር በተያያዘ ማናቸውም ሰው በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 1 መሰረት እውቅና ከተሰጣቸው ከሦስቱ የጋብቻ መፈፀሚያ ስርዓቶች፡- ከክብር መዝገብ ሹም፣ ከኃይማኖት ወይም በባህል መሰረት ከሚፈፀሙ የጋብቻ መንገዶች መካከል በመረጠው ዓይነት በአንዱ የጋብቻ መፈፀሚያ ስርዓት ጋብቻውን መፈፀም የሚችል ቢሆንም የተፈፀመውን ጋብቻ ፍቺ እና የፍቺውን ውጤት ተከትሎ በተጋቢዎች መካከል የሚነሱትን ክርክሮች ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ለፍ/ቤቶች ብቻ የተሰጠ ነው፡፡

ይህም ስልጣን ለፍ/ቤቶች ብቻ የተሰጠበት ዋነኛ ዓላማ ጋብቻ የቤተሰብ መሰረት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በተጋቢዎች መካከል የነበረው ጋብቻ በፍቺ በሚቋረጥበት ጊዜ ፍቺውም ሆነ የፍቺው ውጤት በማህበረሰቡ እና በሀገር ላይ ሊያደርስ የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ ግምት ውስጥ ገብቶ ተጋቢዎች ጋብቻቸውን ለማቋረጥ ከፈለጉ የፍቺ አቤቱታቸውንም ሆነ የፍቺ ውጤቱን ተከትሎ የሚነሱ ክርክሮችን ለፍ/ቤት እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡ ይህ ማለት ጋብቻ የቤተሰብ መሰረትና አልፎም የማሕበረሰቡ መሰረት በመሆኑ በቀላሉ እንዳይፈርስ እና በተቻለ መጠን ፀንቶ እንዲቆይ ለማድረግ ተብሎ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 85 በጋብቻ ውስጥ የተፈሩ ንብረቶችን በተመለከተ ጋብቻው በፍቺ ከፈረሰ በኋላ ፍርድ ቤት በንብረቶቹ ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ ተደንግጓል፡፡ ይህ የቤተሰብ ሕጉ ድንጋጌ የሚያመለክተው ተጋቢዎች በጋብቻ ውስጥ እያሉ በጋራ ያፈሩትን ንብረት እንዲከፋፈሉ የሚከለክል ሲሆን ዓላማውም ጋብቻ ፀንቶ ባለበት ጊዜ በጋብቻ ውስጥ የተፈራ ንብረት ክፍፍል የሚደረግ ከሆነ ጋብቻው እንዲፈርስ በር ይከፍታል የሚል አንድምታ ያለው ድንጋጌ መሆኑን ነው፡፡

ከዚህም አልፎ መንግሥት ጋብቻን የመጠበቅ ግዴታውን ለመወጣት ሲባል የቤተሰብ ሕጉ ካስቀመጣቸው ግዴታዎች መካከል በአንቀጽ 56 ባል ለሚስቱ፣ሚስት ለባልዋ ታማኝ የመሆን ግዴታ፣በአንቀጽ 62፣63 እና 66 በጋብቻ ውስጥ የተገኘ ንብረት የጋራ ንብረት ስለመሆኑና በተጋቢዎች በጋራ እንደሚተዳር፣ በአንቀጽ 68 ያለ ተጋቢዎች ስምምነት የጋራ ንብረትን ወደ ሶስተኛ ሰው ማስተላለፍ እንደማይቻል እንዲሁም በጋብቻ ውስጥ የተፈሩት ንብረቶችን በተመለከተ ጋብቻው በፍቺ ከፈረሰ በኋላ የፍቺውን ውጤት በሚመለከት ፍርድ ቤት ውሳኔ እንደሚሰጥ፡፡ በሌላ በኩል  ለጋብቻ የበለጠ ጥበቃ ለማድረግ ሲባል መንግሥት በወንጀል ሕጉ በጋብቻ ላይ የሚፈጸሙ ድርጊቶች ወንጀል ስለመሆናቸው ከአንቀጽ 646 እስከ 653 ሕግ አውጥቷል፡፡ በዚህ መሰረት አመንዝራነት፣ጋብቻ ላይ ጋብቻ፣በዘመዳሞች መካከል የሚደረግ ጋብቻ እና ያለዕድሜ ጋብቻ የሚሉት ድርጊቶች ወንጀል ስለመሆናቸው በወንጀል ሕጉ ውስጥ ሽፋን እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

ተጋቢዎች የፍቺ አቤቱታ በሚያቀርቡበት ጊዜ የግድ በፍ/ቤቶች በኩል ካልሆነ በቀር ጋብቻን ከማፍረስ ይልቅ ጋብቻው ፀንቶ ሊቆም የሚችልበትን እና ተጋቢዎች በጋብቻ ውስጥ ያለባቸውን የተለያዩ ግዴታዎች እየተወጡ የሚኖሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ ሲሆን፣ ይህም ሁኔታ ባልተሳካበት ጊዜ ከፍቺ ውጤት በኋላ ተፋቺዎች የህፃናት ልጆቻቸውን አስተዳደግ እና የንብረት ክፍፍልን የሚመለከቱ ጉዳዩችን ሊያነሱ ስለሚችሉ በቤተሰብ ሕጉ ጋብቻ ሊፈርስ ከሚችልባቸው ሁኔታዎች እና በጋብቻ ውስጥ የተፈራው ንብረት ክፍፍል ተብለው ከተገለፁት ሕጋዊ ምክንያቶች ተብለው በሕግ ከተደነገጉት ውጪ ለፍቺ ሌላ አዲስ  ምክንያት መጨመር እንደማይቻል ከቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 ድንጋጌ መረዳት ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ የቤተሰብ ሕጉ ከላይ በአንቀጽ 75 በተለየ ሁኔታ ካስቀመጣቸው የጋብቻ ማፍረሻ ምክንቶች ውጪ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሕጉ ከተቀመጠው የፍቺ ምክንያቶች ውጪ ተጋቢዎች ለረዥም ጊዜ ተለያይተው ከኖሩ ጋብቻቸው በሁኔታ እንደ ፈረሰ ይቆጠራል በማለት በሕግ ትርጉም አማካኝነት ሌላ የፍቺ ምክንያት አስቀምጧል፡፡ ተከራካሪዎችም ውሳኔው ጋብቻ በተለየ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር በዘፈቀደ ለጋብቻ ማፍረሻ ምክንያት ማምጣት ሕገ መንግሥቱ ለጋብቻ የሚያደርገውን ጥበቃ ይጥሣል በማለት በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አቅርበዋል፡፡

ጉባዔውም ጉዳዩን አጣርቶ ለፌዴሬሽን ም/ቤት ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ም/ቤቱ በ5ኛ የሥራ ዘመን፤ አምስተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም በመ/ቁ 49/10 ላይ በአመልካች ወ/ሮ አያልነሽ ሞገስ እና በተጠሪ አመልማል አሳየ መካከል ከሚስትነት ይረጋገጥልኝ ጋር በተያያዘ በፍ/ቤቶች ያደረጉትን ክርክር አስመልክቶ የአመልካች ጋብቻ በተለየ ሁኔታ በሕጉ ከተቀመጠው ምክንያት ውጪ ተጋቢዎቹ ለረዥም ጊዜ ተለያይተው በመኖራቸው ጋብቻቸው በሁኔታ ፈርሷል በማለት በፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ ሕገ መንግሥቱ ለጋብቻ ከሚያደርገው ጥበቃ አንፃር ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናል በማለት አስገዳጅ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡