አጣሪ ጉባዔው በ28 ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
March 31, 2023
ማንኛውም ሰው የፈፀመው ድርጊት በወንጀል ሕግ ጥፋት መሆኑ ካልተደነገገ በስተቀር አይቀጣም !
April 19, 2023
Show all

ጉባዔው በ12 የአቤቱታ መዝገቦች ተወያይቶ ሶስቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም ሲል እንዲዘጉ ወሰነ።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሐሙስ ሚያዝያ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ሰፊ ክርክርና ውይይት ካደረገ በኋላ 3 የሕገ መንግሥት አቤቱታዎች እንዲዘጉ ወስኗል። በሌላ በኩል 9 የአቤቱታ መዝገቦች በተጠሪዎች መልስ እንዲሰጥባቸው ውሳኔ አሳልፏል። መልስ እንዲሰጥባቸው ጉባዔው አቅጣጫ ካስቀመጠባቸው የአቤቱታ መዝገቦች መካከል  3ቱ “በሁኔታ የተደረገ ፍቺ” በሚል በፍ/ቤቶች የተወሰኑ ጉዳዮችን የሚመለከቱ እና ይኸን ተከትሎ በይርጋ ቀሪ ስለሚደረጉ የንብረት መብቶችን በተመለከተ ሲሆን ለተጨማሪ መረጃ በተጠሪዎች መልስ እንዲሰጥ ተብሏል። በሌላ በኩል ያለ ጋብቻ እንደ ባል እና ሚስት አብረው የኖሩ ሰዎች የሚያነሱት የንብረት ይገባኛል ክርክር ከሕገ መንግሥቱ አንፃር በምን አግባብ መስተናገድ አለበት በሚለው ላይም ምላሽ እንዲሰጥበት አቅጣጫ ተቀምጧል።

ከዚህ በተጨማሪም በክርክር ተሳታፊ መሆን የነበረባቸው ባለመብቶች ጉዳይ እና የዳኞች ሥልጣን እስከምን ድረስ ነው በሚለው ጉዳይ ምላሽ እንዲሰጥበት አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን በትግራይ ክልል በማሕበራዊ ፍ/ቤት በሚደረግ ክርክር “በጠበቃ መወከልን የሚከለክልበት” አግባብ የዜጎችን ፍትህ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ከማክበር አኳያ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ምላሽ እንዲሰጥበት ተብሏል።

በመጨረሻም ጉባዔው በቋሚ ንብረት ይገባኛል ክርክር ሕጋዊ ማስረጃ እና ሰነድ ያለውን ተከራካሪ ወገን “ማስረጃውን ቀሪ ማድረግ ስለመቻል አለመቻሉ” ምላሽ እንዲሰጥበት እንዲሁም የወንጀል ክርክርን በተመለከተ የተከሳሽን “ነፃ ሆኖ የመገመት” ሕገ መንግሥታዊ መብት ከማስጠበቅ እና አቃቢ ሕግ የሚያቀርበው ማስረጃ  “ከጥርጣሬ በላይ አሳማኝ እና በቂ” መሆን ስለሚኖርበት አግባብ አቃቢ ሕግ ምላሽ እንዲያቀርብ ጉባዔው አቅጣጫ አስቀምጧል።