ጉባዔው 137 ሕገ መንግሥታዊ አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
September 22, 2022
ክብርት ሰብሳቢዋ በዓለም አቀፉ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና የመሰል ተቋማት ኮንፈረንስ ላይ አፍሪካን በመወከል ፅሑፍ አቀረቡ
October 12, 2022

ጉባዔው 35 የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም(አዲስ አበባ)

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ቀደም ሲል በጉባዔና በንዑስ ጉባዔ ደረጃ ሲመረምራቸው ከቆያቸው አቤቱታዎች መካከል በአንድ ጉዳይ ላይ የሕገ መንግሥት ጉዳይ እንዳለበት እምነት በማሳደሩ ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሃሳብ ከመስጠቱ በፊት በጉባዔው “የጉዳዮች አቀራረብና አወሳሰን መመሪያ” መሰረት ለተጨማሪ ማጣራት ተጠሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ 32 ጉዳዮች ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት የለባቸውም በሚል ረቡዕ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ሌሎች ሁለት ጉዳዮችን ደግሞ ለተጨማሪ ማጣራት ወደ ባለሙያዎች መልሷቸዋል፡፡

ተጠሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ ትዕዛዝ የስተላለፈበት ጉዳይ የኦሮሚያ የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 130/90 ላይ መሰረት በማድረግ ስለገጠር መሬት ውርስ የቀረበ ሕገ መንግሥታዊ  የትርጉም አቤቱታ ሲሆን አዋጁ የልጅ ልጆች የአያቶቻቸውን መሬት በቁም በስጦታ ካላገኙ በስተቀር ወላጆቻቸው ቀድመው ከሞቱ የወላጆቻቸው ተተኪ ሆነው ከቀሪ ልጆች(አክስት እና አጎት) ጋር የመውረስ መብት የላቸውም ይላል፡፡  ከዚህ አንፃር ልጆች የሚለው ከሕገ መንግሥቱ አንፃር እንዴት ይተረጎማል የሚለውን ጉባዔው በስፋት ከተወያየበት በኋላ በአቤቱታው ላይ የሕገ መንግሥት ጉዳይ እንዳለበት እምነት በማሳደሩ ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሃሳብ ከመስጠቱ ለተጨማሪ ማጣራት ተጠሪዎች ምላሽ እንዲሰጡበት ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡

ተጨማሪ ማጣራት እንዲደረግባቸው አቅጣጫ ከተሰጠባው ጉዳዮች ውስጥ አንደኛው ኃይማኖታዊ ጉዳይን የሚመለከት ሲሆን ከሸሪዓ ፍ/ቤት አልፈው በመደበኛ ፍ/ቤት የሚታዩ ጉዳዮች ከሕገ መንግስቱ አንፃር እንዴት ይስተናገዳሉ በሚል በጉባዔው ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ለተጨማሪ ማጣራት ከሀይማኖት ተቋማቱ ተጨማሪ ሀሳብ እንዲሰጥበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ 

ሁለተኛው የመሬት ውርስ ሕገ መንግሥታዊ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ከ32 ዓመታት በፊት አባታቸው የሸጡትን መሬት ልጆች “መሬት መሸጥ መለወጥ አይቻልም” በሚለው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት የውርስ ይገባናል በማለት የሽያጭ ውሉ ፈርሶ መሬቱ ተመላሽ ይሁንልን በሚል ያቀረቡት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄን የሚመለከት ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይም የተለያዩ አስተያየቶች ከጉባዔ አባላት የተነሱ ሲሆን መሬት ሻጩ (የውርስ ጠያቂዎች አባት) እና ገዥው “መሬት መሸጥ መለወጥ አይቻልም” የሚለውን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ ስለጣሱ መሬቱ የሁለቱም ሳይሆን የመንግሥት መሆን አለበት የሚለው አንደኛው መከራከሪያ ሲሆን፤ የውርስ ጠያቂዎች አባት በሕይወት እያሉ መሬቱን ከሕግ እውቅና ውጭ ሸጠውም ቢሆን ቤትና ሌሎች ቋሚ ንብረቶች ሲፈሩ ዝም ስላሉ ፈቅደው እንደሰጡ ስለሚቆጠር መሬትነቱ ቀርቶ በመሬቱ ላይ የተፈሩት ንብረቶች ስለሚገኙበት የውል ይፈረስልን ጥያቄው ውድቅ መደረግ አለበት የሚለው ሌላኛው መከራከሪያ ሆኖ ቀርቧል። ከዚህ ውጭ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች በተቃራኒ የተፈፀመን የመሬት ሽያጭ እውቅና መስጠት እንደማይቻል ነገር ግን ጉዳዩ በይርጋ ቀሪ ሊደረግ የሚችልበት አግባብም መታየት ይኖርበታል የሚል አማራጭም ቀርቧል። በመጨረሻም ተጨማሪ ማስረጃዎች ተመርምረው ግራ ቀኙ መብት አለኝ የሚሉበት አግባብ ታይቶ ለቀጣይ ጉባዔ ዳብሮ እንዲቀርብ አቅጣጫ ተሰጥቷል።