የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽ/ቤት አመራሮችና ሠራተኞች ለጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ደም ለገሱ።
September 20, 2022
ጉባዔው 35 የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
September 30, 2022

ጉባዔው 137 ሕገ መንግሥታዊ አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

????????????????????????????????????

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ለረዥም ጊዜያት በዋና እና በንዑስ ጉባዔ ሲያጣራቸውና  ሲመረምራቸው ከቆየባቸው 137 የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታ ዎች  መካከል 134 የሚሆኑት የሕገ መንግሥት ጥሰት የለባቸውም በማለት የወሰነ ሲሆን ሶስት ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ማጣራት እንዲደረግባቸው ውሳኔ አሳልፏል።

ጉባዔው ረቡዕ መስከረም 11 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ቀደም ሲል በንዑስና በዋና ጉባዔ በተለያዩ ጊዜያት የመረመራቸውንና እና ሰፊ ማጣራት ያደረገባቸውን 134 አቤቱታዎችን የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም ብሎ ከመወሰኑ ባሻገር በሦስት አቤቱታዎች ላይ ተጨማሪ ማስረጃና ጥናት ተደርጎ ለቀጣይ ጉባዔ እንዲቀርቡ ወስኗል።

ከነዚህም መካከል የመጀመሪያው ጉዳይ በወንጀል ምርመራ ወቅት በኤግዚቢትነት የተያዘ ንብረት ማስመለስን የሚመለከት ሲሆን በወንጀል የተጀመረው የክርክር ሂደት በተጠሪዎች ስህተት እና ምስክሮቻቸው ባለመቅረባቸው ውሳኔ ሳያገኝ በመቅረቱ አመልካች ንብረቶቻቸው እንዲመለሱላቸው ያቀረቡት የፍትሃብሄር ክስ ከሁለቱ ፍ/ቤቶች ትእዛዝ አኳያ ተገቢነት አለው የለውም የሚለው ላይ ጉባዔው ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ በኤግዚቢት የተያዘው ንብረት በክስ ዝርርዝርሩ ውስጥ መካተት ያለመካተቱን እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ማስረጃዎች ተጣርተው ለቀጣይ ሳምንት ስብሰባ  እንዲቀርብ ወስኗል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ የገጠር መሬት የውርስ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሲሆን የአቤቱታው መነሻ ጥያቄ አውራሽ ከአመልካቾች ወላጆች በኋላ ስለሞቱ በእነርሱ እግር በተተኪ ወራሽነት ሟች አያታቸውን መውረስ አትችሉም በመባላቸው የቀረበ አቤቱታ ነበር። በዚህም ላይ የገጠር መሬት አጠቃቀምን በተመለከተ ሕገ መንግስቱ ሊጠብቅ የፈለገው መብት የማንን ነው? ልጅነት ከገጠር መሬት አጠቃቀም አንፃር እንዴት ይተረጎማል? መሬትን መውረስ የሚችለው ማን ነው? ክልሎች በአዋጅና በደንቦቻቸው ያወጧቸው የገጠር መሬት ሕገ መንግሥታዊ  መብቶች ከሕገ መንግሥቱ መንፈስ አንፃር እንዴት እየተተረጎሙ ነው? በሚሉና በሌሎች ነጥቦች ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ከገጠር መሬት አጠቃቀም አንፃር የተዘጋጁ ጥናቶችና የክልል አዋጆችና ደንቦች መረጃዎች ተጣርተውና ተካተው  ለቀጣይ ሳምንት ስብሰባ  እንዲቀርብ ወስኗል፡፡

የመጨረሻው አቤቱታ የጋብቻ-ፍቺ ውጤትን ተከትሎ የሚደረግን የንብረት ክፍፍል በሚመለከት ንብረቱ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ንብረት መሆኑ በተለየ ማስረጃ ሳይረጋገጥ አመልካችን ከንብረቱ ተከራካሪዎቹ እኩል ተካፋይነት በማስወጣት የተወሰነው ውሳኔ በመብቴን ጥሷል ሲል የቀረበ አቤቱታ ነው፡፡ በዚህም ጉባዔው  በሕግ ባልተካተቱ ጉዳዮች የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ም/ቤት ግንቦት 30/2013 ዓ.ም 5ኛ የፓርላማ ዘመን 6ኛ አመት ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በሰጠው ውሳኔ በጋብቻ ወቅት የተፈራ ንብረት የጋብቻ ፍቺ ሲፈጸም በተለይ ባል ሁለት እና ከሁለት በላይ ጋብቻ ሲኖረው አንዱ ጋብቻ በፍቺ ሲፈርስ እና የጋብቻ ፍቺን ተከትሎ የንብረት ክፍፍል ሲደረግ የንብረቱ ተካፋዮች እኩል መብት ይኖራቸዋል በሚል የወሰነውንና በዚህ ጉዳይ ላይ የቀረቡትን የፍ/ቤቶቹ ውሳኔ በመመልከት ይህ ጉዳይ ከፌዴሬሽን ም/ቤት  ውሳኔ ጋር ተመሳሳይነት አለው የለውም?  ፍ/ቤቶቹ ይህን ጉዳይ ሲወስኑ መነሻቸው ምንድን ነው? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ለተነሱት ጥያቄዎች ተጨማሪ ማስረጃ እና ጥናት ተደርጎባቸው ለቀጣይ ጉባዔ እንዲቀርቡ አቅጣጫ ተቀምጧል።