የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ላይ የባለሙያዎች ማብራሪያ
May 21, 2020
ጉባኤው ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሰጠ
June 1, 2020

ጉባዔው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርንና የምርጫ ቦርድን አስተያየት አደመጠ

ጉባዔው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርንና የምርጫ ቦርድን አስተያየት አደመጠ

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ያለፉት ሁለት ቀናት አስተያየት የማድመጥ (Hearing) ስነ ሥርዓት ቀጣይ በሆነው በዛሬው ግንቦት 13/2012 ፕሮግራም ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርንና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችን በሸራተን አዲስ ሆቴል እንዲገኙ በመጋበዝ ሀሳባቸውን አደመጠ።

በስነ ሥርዓቱ ላይ በጤናው ዘርፍ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ለያ ታደሰ፣ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ እና የኮቪድ 19 የሳይንስ አማካሪ ካውንስል አባል የሆኑት ፕሮፌሰር የማነ ብርሀኔ ስለ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና ስለሚያስከትለው ተፅዕኖ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ፕሮፌሰር የማነ እንዳስረዱት ወረርሽኝ ማለት ከቁጥር ጋር የተያያዘ ሳይሆን ማየት የሌለብንን በሽታ በእንስሳ ላይ እንኳ ከታየና ወደ ሰው ሊመጣ ይችላል ተብሎ ከታሰበ ያ በሽታ ወረርሽኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተለምዶ የሕዳር ወረርሽኝ ተብሎ የሚታወቀው “Spanish Flue” በዓለም 50 ሚሊዮን ገደማ በኢትዮጵያም በርካታ ሰዎችን ገድሎ በወቅቱ በሀገራችን የመንግሥት ሥራ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ቆሞ እንደነበር አስታውሰው፣ አንድ ወረርሽኝ በማኅበረሰቡ ውስጥ አንድ ሰው ተገኘ ማለት ሌሎች በርካታ ሰዎች አሉ ተብሎ ነውና የሚታሰበው አሁን ጠንክረን ካልሠራን የበሽታው አስጊነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሊያ በበኩላቸው ምንም የጉዞም ሆነ የንክኪ  ታሪክ የሌላቸው ሰዎች በበሽታው መያዛቸው በሽታው በማኅበረሰቡ ውስጥ እየተሰራጨ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል፡፡ ኮቪድ 19 ከሌላው ወረርሽኝ በተለየ ሁኔታ ከሰው ወደ ሰው በንክኪ ብቻ በከፍተኛ ደረጃ የሚሰራጭ መሆኑን ጠቁመው፣ ከገዳይነቱ ባሻገር የሚፈጥረው የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ቀውስ አስከፊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ዶ/ር ኤባም ጨምረው ሲያስረዱ በሽታው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እንደ እኛ ደሃ የሆኑ ሀገራት ያላቸው ብቸኛ መፍትሄ መከላከል እንደሆነና ለዚህም የሕዝብ መሰባሰብን ማስቀረት አንዱና ዋነኛው መፍትሄ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በበሽታው ምክንያት ምርጫው ስለመራዘሙ ምን አስተያየት አላችሁ ተብለው ከጉባዔው አባላት ጥያቄ የተነሳላቸው ዶ/ር ሊያ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ሲመልሱ፣ ቅድሚያ ለሚሰጠው ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶ ካልተሠራ በሽታው በኅበረተሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት እንደሚያደርስ ጠቁመው፣ ምርጫው ይደረግ ከተባለ በበሽታው ምክንያት የተጣሉ ገደቦች ይላላሉ ማለት ነው ብለዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ “ቤተሰቦቻችን በበሽታ ሲያልቁ ማየት ወይም የተወሰነ ጊዜ እንታገስ” ወደሚል ምርጫ እንገባለን ሲሉ የጉዳዩን አንገብጋቢነት አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም በሽታው ከዚህ እየከፋ የሚሄድ ከሆነ ተጨማሪ እርምጃዎችና ገደቦች ሊያስፈልጉ ይችላሉ በማለት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

በምርጫ ቦርድ በኩል ሰብሳቢዋ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳና ምክትላቸው አቶ ውብሸት አየለ የተገኙ ሲሆን፣ በአቶ ውብሸት አማካይነት አጠቃላይ የምርጫውን ዝግጅት ሂደትና በበሽታው ምክንያት ምርጫውን ማከናወን ያለመቻሉን የተመለከተ ዝርዝር ጉዳይ በንባብ ቀርቧል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ ማናቸውንም ምርጫና ሕዝበ ውሳኔዎችን የማድረግ ኃላፊነት የምርጫ ቦርድ መሆኑ የጠቆሙት አቶ ውብሸት፣ ምርጫው ከተራዘመበት ጊዜ ጀምሮ ሂደቱን ዲጂታል ለማድረግ የዳታ ቤዝ ግንባታ እንዲሁም የሚዲያ ክትትል ለማድረግ የሚያስችሉ የመሳሪያ ግዢዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንና ሌሎችም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመቀጠልም ቦርዱ ምርጫውን ለማራዘም እንደ ምክንያት የተጠቀመው ምን እንደሆነ በግልፅ እንዲያስረዳ በጉባዔው በተጠየቀው መሰረት ወ/ሪት ብርቱካን ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የሕዝብን ደህንነት ለመጠበቅ የተወሰዱት እርምጃዎች ምርጫውን ለማድረግ የማያስችሉን መሆኑን ስለተረዳን ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስነው ካሉ በኋላ፡- ምርጫውን አሳታፊ፣ ግልፅና ነፃ ለማድረግ የተጣሉት ገደቦች የሚያስችሉ አይደሉም ብለዋል፡፡ አያይዘውም ገደቡ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ ከሆነ በማለት እንደምንም አጠጋግተን ምርጫውን ለማከናወን አስበን ነበር ያሉት ኃላፊዋ፣ ችግሩ በአጭር ጊዜ እንደማይቆም ከጤና ባለሙያዎች ሲነገረን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳባችንን ለማቅረብ ተገደናል በማለት አስረድተዋል፡፡ ከጉባዔ አባላት ሌሎችም በርካታ ተያያዥ ጥያቄዎች ለኃላፊዎቹ ተነስተውላቸው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል፡፡

በመጨረሻም ለሦስት ቀናት በቀጥታ የሚዲያ ስርጭት ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ከምርጫ መራዘም ጋር በተያያዘ ሲከናወን የነበረው አስተያየት የማድመጥ (Hearing) ስነ ሥርዓት መጠናቀቁን የገለፁት የጉባዔው ሰብሳቢ ወ/ሮ መዓዛ፣ በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉትን ሁሉንም አካላትና የሚዲያ ተቋማትን አመስግነዋል፡፡ ስነ ሥርዓቱንም የተሳካና ለሀገራችን የዴሞክራሲና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ዕመርታን የፈጠረ ክስተት ነው በማለት ገልጸውታል፡፡