ማንኛውም ሰው የፈፀመው ድርጊት በወንጀል ሕግ ጥፋት መሆኑ ካልተደነገገ በስተቀር አይቀጣም !
April 19, 2023
የመጀመሪያው የአፍሪካ እንስት ዳኞች ጉባዔ በጋቦን ሊብረቪሌ እ.ኤ.አ ከግንቦት 2 እስከ 6 ቀን 2023 ተካሄደ።
May 10, 2023
Show all

ጉባዔው ከቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ላይ የመስማት /Public Hearing/ ስነ ሥርዓት አካሄደ

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በአዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀፅ 9 መሰረት ለሕገ መንግሥት ትርጉም በቀረበ ጉዳይ ላይ ከጉዳዩ ጋር ተያየዥነት ያላቸውን አካላትና ባለሙያዎችን እንደአስፈላጊነቱ በጉዳዩ ላይ የመስማት ስነ ሥርዓት ሊያካሂድ እንደሚችል በተገለፀው መሰረት ሚያዝያ 21/2015 ዓ.ም ይህንኑ ተግባር አከናውኗል።በመስማት ሂደቱ መነሻ ላይ የጉባዔው ሰብሳቢ ክቡር አቶ ቶዎድሮስ ምህረት እደገለፁት የመስማት ስነ ሥርዓቱ በጉባዔው ታሪክ ሁለተኛው ሲሆን የመጀመሪያው (በኮቪድ ምክንያት ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫን ማድረግ ባለመቻሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለትርጉም የቀረበው ጉዳይ) ሲሆን፣ አሁን እየተካሄደ ያለው ደግሞ ተከራካሪ ወገኖች በተገኙበት በመካሄዱ የመጀመሪያው ያደርገዋል ብለዋል።ይህንን ካሉ በኋላ ተከራካሪ ወገኖች የክርክራቸውን ጭብጥ እንዲያስረዱ መድረኩን ክፍት ባደረጉት መሰረት በቅድሚያ አቤቱታ አቅራቢ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝን በመወከል ከከተማ አስተዳደሩ ፍትህ ቢሮ የመጡ አቃቤያነ ሕግ የሆኑት ሃሳባቸውን አሰምተዋል።አቃቢ ሕጎቹ በወቅቱ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተብሎ የሚጠራው የፌዴራል ተቋም ከ40/60 የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 21/2015 የአዲስ አበባ ከተማን የራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚጋፋ በመሆኑ ከመነሻው ሕጋዊነት የለውም ብለዋል። በተለይም የመመሪያው አንቀፅ 16/2 100% ለከፈሉ ቅድሚያ ይሰጥ ማለቱ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሊሰጥልን ይገባል ሲሉ ሃሳባቸውን አሰምተዋል።በመቀጠል ተጠሪዎችን በመወከል የተገኙ ጠበቆች በተመሳሳይ ሀሳባቸውን አሰምተዋል። በጠበቆቹ በኩል በቀረበው መከራከሪያ እንደተገለፀው ጉዳዩ የ21 ሺህ ሰዎችን መብት የያዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወደ ፍርድ ቤት ፍትህ ፍለጋ የመጡ 761 ሰዎችን በመወከል እንደተገኙ ተናግረው፣ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ዜጎች መንግሥትን አምነውና ያወጣውን መመሪያ ተማምነው በብድር ጭምር ዕዳ ውስጥ ገብተው 100% በቆጠቡት ገንዘብ የተገነባ ቤትን አይገባችሁም ማለት ፍትሃዊ አለመሆኑን አንስተዋል። በሕገ መንግሥቱ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ መንግሥት ነው የሚል በመሆኑ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያወጣውን መመሪያ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ሊያደርገው አይችልም ሲሉም ተከራክረዋል። ከስር ፍርድ ቤት እስከ ሰበር በነበረውም ክርክር ፍርድ ቤቶቹ ሕግን መሰረት አድርገው በመመሪያው መሰረት የወሰኑልን በመሆኑ ጉባዔውም ይህንን በማድረግ የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት ሊያስከብር ይገባል ሲሉ ሀሳባቸውን አሰምተዋል።ከተከራካሪ ወገኖች ሀሳብ መደመጥ በኋላ በገለልተኝነት ሙያዊ አስተያየት በጉዳዩ ላይ ለመስጠት ከተጋበዙ ባለሙያዎች መካከል በፅሑፍ ለጉባዔው ካስገቡት በተጨማሪ፣ በአካል የተገኙ 5 ያህል የሕግ ባለሙያዎችና ምሁራን ከሕገ መንግሥቱ እና ከነባራዊ ሁኔታው ጋር በማያያዝ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ምሁራዊ አስተያየት አሰምተዋል።በመጨረሻም ከጉባዔው አባላት ለተከራካሪ ወገኖች የተለያዩ የማጥራት ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ካብራሩ በኋላ፣ በአጭር ቀን ውስጥ ጉባዔው ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ በሰብሳቢው ተገልፆ የመስማት /Public Hearing/ ስነ ሥርዓቱ ተጠናቋል።