አጣሪ ጉባዔው በበጀት ዓመት ዕቅዱ ላይ ውይይት አደረገ።
September 13, 2023
ጉባዔው በ108 አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ሰጠ።
September 25, 2023
Show all

ጉባዔው በ71 የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ላይ ውሳኔ ሰጠ።

????????????????????????????????????

. ሁለት ጉዳዮች ላይ  የሕገ መንግሥት ጥሰት ስላገኘባቸው ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት  ለፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላኩ ወሰነ።

ጳጉሜ 3 ቀን 2015 ዓ.ም (አዲስ አበባ)

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሐሙስ ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በንዑስ ጉባዔ እና በዋና ጉባዔ ደረጃ ውይይትና እና ምርመራ ሲደረግባቸው በቆዩ 71 የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል።

ጉባዔው በዕለቱ ከቀረቡለት 71 የትርጉም አቤቱታ መዛግብት መካከል ሁለት ጉዳዮች ላይ  የሕገ መንግሥት ጥሰት ስላገኘባቸው የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላኩ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል።

63 የአቤቱታ መዛግብት ሕገ መንግሥት ትርጉም የማያስፈልጋቸው ሆነው በማግኘቱ እንዲዘጉ ወስኗል።  እንዲዘጉ ከተወሰኑ 63 አቤቱታዎች መካከል 4ቱ አከራካሪ የነበሩ ነገር ግን በጉባዔው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው የሕገ መንግሥት ጥሰት የለባቸውም የተባሉ ሲሆኑ 2ቱ ማስረጃ ባለማሟላታቸው እንዲዘጉ የተወሰኑ እንዲሁም ሌሎች 57 የትርጉም አቤቱታዎች የሕገ መንግሥት ጥሰት የለባቸውም በሚል በጉባዔው ውሳኔ ያገኙ ናቸው።

በሌላ በኩል በዕለቱ ከቀረቡት የአቤቱታ መዛግብት ውስጥ በስድስቱ የሕገ መንግሥት የትርጉም ጥያቄ መዛግብት ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ በተጠሪ መልስ እንዲሰጥባቸውና በድጋሚ እንዲቀርቡ በጉባዔው ተወስኗል።

ጉባዔው ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት የውሳኔ ሃሳብ እንዲቀርብ ከወሰናቸው ጉዳዮች አንዱ በመዝገብ ቁጥር 6725/14 የቀረበ የንብረት ሕገ መንግሥታዊ መብት ክርክር ሲሆን ክርክር የተደረገበት ቤት ከአዋጅ ቁጥር 47/67 ውጪ በመንግሥት የተያዙ ቤቶችን በሚመለከት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ በቀን 29/01/2011 ዓ.ም በወሰነው መሰረት ከአዋጁ ውጪ ስለመሆኑ ስልጣን በተሰጠው አካል እስካልተረጋገጠ ድረስ ለረዥም ግዜ በመንግስት ቁጥጥር ስር ሲተዳደር የነበረ ቤት የመንግስት እንደሆነ ግምት የሚወሰድ በመሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቀን 29/07/2014 ዓ.ም በመ/ቁ. 212441 አከራካሪው ቤት ለተጠሪዎች እንዲመለስ የሰጠው ውሳኔ ከሕገ መንግስቱ ጋር ይቃረናል በሚል ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላክ ወስኗል፡፡

በመዝገብ ቁጥር 3225/10 የቀረበው ሁለተኛው ጉዳይ የባልና ሚስት ንብረት ክርክርን የሚመለከት ሲሆን  አመልካች ሟች ባለቤቴ ከዚህ አለም በሞት እስከተለዩበት ቀን ድረስ የነበረን ጋብቻ ቀጥሎ የነበረ ስለመሆኑ ማስረጃ አቅርቤ እያለሁ በሁኔታ ፍች ተፈፅሟል መባሉ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 34 የተቀመጠውን መብቴን ይጥሳል ብለው አቅርበዋል፡፡ ጉባዔውም በጉዳዩ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 138073 በቀን 25/07/2010 ዓ.ም አመልካች ከሟች ጋር የነበራቸው ጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል ሲል የሰጠው የሕግ ትርጉም ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን በመሆኑ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሠረት ተፈጻሚነት የለውም በሚል የመጨረሻ ትርጉም እንዲሰጠው ለፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላክ ወስኗል፡፡