ጉባዔው በ10 ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
April 21, 2022
አርሶ አደሮች ከመሬት ይዞታቸው ተፈናቅለዋል የሚባለው መቼ ነው?
May 20, 2022

ጉባዔው በ36 ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ በ35ቱ ላይ ውሳኔ አሳለፈ

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሐሙስ ግንቦት 11 ቀን 2014 ባካሄደው ስብሰባ 36 የተለያዩ ጉዳዮችን መርምሮ ሠላሳ አምስቱ ጉዳዮች የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በማለት ውሳኔ ሲያሳልፍ አንዱን ጉዳይ ለተጨማሪ ምርመራ አሳድሮታል።

ጉባዔው ጉዳዮቹን በመረመረበት ወቅት ሰላሳ አራቱን ጉዳዮች በሙሉ ድምፅ ትርጉም አያስፈልጋቸውም በማለት የወሰነ ሲሆን፣ አንዱ ጉዳይ ግን ሰፊ ውይይትና ክርክር ተደርጎበት በመጨረሻ ድምፅ እንዲሰጥበት ተደርጎ በአብላጫ ድምፅ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልገውም ሊባል ችሏል።

አከራካሪ ሆኖ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ጉዳይ ከውርስ ጋር በተያይዞ ባለጉዳይ የሆኑት አመልካች በፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 40 የተደነገገውን የንብረት መብቴን የሚጥስ በመሆኑ ጉባዔው የሕገ መንግሥት ትርጉም ይስጥልኝ በማለት ያመጡት ነው።

አመልካች ከባለቤታቸው ጋር በነበሩበት ጊዜ ከሟች ባለቤታቸው ቤቱን በስጦታ በሰነዶች ማረጋገጫ በውል ያገኙት መሆኑን ጠቅሰው ወራሾች ሊካፈሉት አይገባም በማለት ነበር አቤቱታቸውን ያቀረቡት።

ባልና ሚስት በጋብቻ ውስጥ ሲኖሩ ንብረትን በተመለከተ የሚያደርጉት ውል በፍርድ ቤት እስካልፀደቀ ድረስ ውጤት አይኖረውም ወይም ሕጋዊ አይደለም የሚለውን የተሻሻለውን የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 73 በመጥቀስ በአንድ በኩል በጉባዔው የቀረበ ሀሳብ  ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ውሉ በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት እስከተመዘገበ ድረስ ሕጋዊ ነው በሚል ክርክር ሊደረግበት ችሏል።

በመጨረሻም ሰብሳቢው ድምፅ እንዲሰጥበት በማድረግ አብላጫው የጉባዔ አባላት የንብረት ስጦታ ውሉ በፍርድ ቤት እስካልፀደቀ ድረስ ውጤት አይኖረውም የሚለውን በመያዝ የአመልካች አቤቱታ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልገውም የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሷል።