የህፃናት ሕገ መንግሥታዊ መብት ከአሳዳጊዎቻቸው የሃይማኖት ነፃነት አንፃር
August 9, 2022
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ
September 8, 2022

ጉባዔው በ29 ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ 27ቱ ላይ ውሳኔ አሳለፈ

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በዚህ ሳምንት ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ በ27 ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ።

አጣሪ ጉባዔው በመደበኛ ጉባዔው 29 የባለጉዳይ አቤቱታዎችን መርምሮ 27ቱ መዝገቦች የሕገ መንግሥት ጥሰት የሌለባቸው ሆኖ ስላገኛቸው ውሳኔ በመስጠት ዘግቷቸዋል። ቀሪዎቹ 2 መዝገቦች ላይ የሕገ መንግሥት ጉዳይ እንዳለበት እምነት በማሳደሩ ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሃሳብ ከመስጠቱ በፊት በጉባዔው “የጉዳዮች አቀራረብና አወሳሰን መመሪያ” መሰረት ለተጨማሪ ማጣራት ተጠሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ለተጨማሪ ማጣራት ተጠሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ ትዕዛዝ የተላለፈበት ጉዳይ ከ40/60 ቁጠባ ቤቶች ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ አመልካችነት ለጉባዔው የቀረበ አቤቱታ ነው።

ጉዳዩም ከዚህ ቀደም በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በወጣው መመሪያ ቁጥር 21/2005 አንቀፅ 16  እና 2.6 መሰረት “100% ተቀማጭ ያደረጉ ተመዝጋቢዎች ከሌሎች ቅድሚያ ቤት ሊያገኙ እንደሚችሉ ከተቀመጠ በኋላ፣ ያ ሳይሆን ቀርቶ ዕጣ ውስጥ በመካተታችን ቤት ሳናገኝ ቀርተናል” ባሉ አካላትና በኢንተርፕራይዙ መካከል በፍርድ ቤቶች ክርክር ተደርጎ ለአሁን ተጠሪዎች በመወሰኑ ውሳኔው በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 41(3) እና 89(2) ዜጎች በመንግሥት በጀት በሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነትና በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት እንዳላቸው የተደነገገውን የሚጥስ ነው በማለት ትርጉም እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

የሕገ መንግሥት ትርጉም ይሰጥልኝ በማለት በአመልካች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ወደ ጉባዔው በቀረበው አቤቱታ ላይ ጉባዔው ሰፊ ጊዜ ወስዶ ከተወያየና ከተከራከረ በኋላ ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ጉዳይ እንዳለበት እምነት በማሳደሩ ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሃሳብ ከመስጠቱ በፊት በጉባዔው “የጉዳዮች አቀራረብና አወሳሰን መመሪያ” መሰረት ለተጨማሪ ማጣራት ተጠሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ሌላው ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ለጉባዔው የተላከ ጉዳይ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የቀረበ ነው።

በዚህ መዝገብ ተጠሪ ሆነው የቀረቡት የነሌ/ጀኔራል ታደሰ ወረደ እና 74 የቀድሞ የህ.ወ.ሐ.ት አመራርና መኮንኖች ሲሆኑ፣ ፍርድ ቤቱም በከሳሾች የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሊሰጥበት ይገባዋል ያለውን የፌዴራል እና የክልል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን የተመለከተውን ነጥብ በመለየት ወደ ጉባዔው ሊልክ ችሏል።

በዚህም ጉዳይ ጉባዔው ሰፊ ክርክር ካካሄደ በኋላ በጉባዔው “የጉዳዮች አቀራረብና አወሳሰን መመሪያ” መሰረት በጉዳዩ ላይ ተጠሪዎች ምላሽ ይሰጡበት ዘንድ ትዕዛዝ አስተላልፏል።