ጉባዔው በ50 የትርጉም አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እና አቅጣጫ አሰቀመጠ።
January 19, 2024
በጋብቻ ውስጥ ባልና ሚስት የሚያደርጉት የንብረት ስምምነትና ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃው
January 29, 2024
Show all

ጉባዔው በ122 የአቤቱታ መዛግብት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ፣ የውሳኔ ሐሳብና አቅጣጫ አስቀመጠ።

የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሐሙስ ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም  ባደረገው ስብሰባ በንዑስ አጣሪ ጉባዔ እና በአጣሪ ጉባዔ ጽ/ቤቱ የሕግ ተመራማሪዎች ሰፊ ጥናት እና ማጣራት ተደርጎባቸው በቀረቡለት 122 የሕገ መንግሥት የትርጉም አቤቱታዎች  ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔ፣ የውሳኔ ሐሳብ እና አቅጣጫ አስቀመጠ።

በዚህም በዕለቱ ከተመለከታቸው የአቤቱታ መዛግብት ውስጥ 114ቱ የሕገ መንግሥት ጥሰት አልተፈፀመባቸውም በማለት እንዲዘጉ ወስኗል።

በሌላ በኩል የይዞታ የመፋለም ክርክርን እና የእርሻ የመሬት ክርክርን በሚመለከት በቀረቡ  2 አቤቱታዎች ላይ በተጠሪዎች ምላሽ እንዲሰጥባቸው እና ለውሳኔ በድጋሚ እንዲቀርቡ ጉባዔው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

 ከዚህ በተጨማሪም ጉባዔው በዕለቱ ከተወያዬባቸው ጉዳዮች መካከል በአምስት የአቤቱታ መዛግብት ላይ ተጨማሪ ማጣራት እና ምርመራ ተደርጎባቸው ለውሳኔ እንዲቀርቡ ያዘዘ ሲሆን፤ እነዚህ  ተጨማሪ ማጣራት ይደረግባቸው የተባሉ አቤቱታዎች 3ቱ የንብረት ክርክርን የሚመለከቱ ሲሆን ቀሪ 2ቱ ደግሞ የውል ክርክር እና ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 ጋር ተያይዞ በቀረበ መቃወሚያ የተደረጉ ክርክሮችን የሚመለከቱ ናቸው።

በዕለቱ የሕገ መንግሥት ጥሰት ተፈፅሞበታል በሚል ለፌዴሬሽን ም/ቤት የውሳኔ ሐሳቡ እንዲላክ በጉባዔው የተወሰነው ጉዳይ በመዝገብ ቁጥር 3129/10 የቀረበና ከሚስትነት ይረጋገጥልኝ ጋር ተያይዞ የተደረገ ክርክርን ይመለከታል። በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ተወስኖ እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ  በፀናው ውሳኔ፤ ሁለቱ ተጋቢዎች ተለያይተው ስለቆዩ ብቻ ጋብቻው በሁኔታ ፈርሷል በሚል የተሰጠው ውሳኔ የቤተሰብ ሕጉ በአንቀፅ 75 መሰረት ጋብቻ የሚፈርሰው ከተጋቢዎች አንደኛው ሲሞት ወይም  ተጋቢው መጥፋቱ በፍ/ቤት ሲረጋገጥና የመጥፋት ውሳኔ ሲሰጥ፤ ጋብቻ ለመፈፀም መሟላት ካለባቸው ሁኔታዎች አንዱ ስለሚጣስ በሕግ መሰረት ጋብቻው እንዲፈርስ በፍ/ቤት  ሲወሰን እንጅ ተጋቢዎች ተለያይተው ስለቆዩ በሚል በሁኔታ ጋብቻ አይፈርስም በሚል የውሳኔ ሐሳብ ላይ የደረሰው ጉባዔው፤ በዚህ መዝገብ ላይ ፍ/ቤቶች ሕግ አውጪው በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 55 (1) እና 55 (5) መሰረት በተሰጠው ስልጣን መሰረት የሚያወጣቸውን ሕጎች በመተርጎም በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 79 (3) መሰረት የተጣለባቸውን ግዴታ ይወጣሉ እንጂ ሕግ በመተርጎም ሰበብ የሕግ ማውጣት ሚና ሊኖራቸው አይገባም ሲል ውሳኔው የሕገ መንግሥት ጥሰት እንደተፈፀመበት ገልጿል፡፡

ከዚህ  በተመሳሳይ ጉዳይ የፌዴሬሽን ም/ቤት በ 5ኛ የፓርላማ ዘመን፤ አምስተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም በመ/ቁ 49/10 በአመልካች ወ/ሮ አያልነሽ ሞገስ እና በተጠሪ አመልማል አሳየ መካከል ከሚስትነት ይረጋገጥልኝ ጋር በተያያዘ በፍ/ቤቶች ያደረጉትን ክርክር አስመልክቶ ፍ/ቤቶች የአመልካች ጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል በማለት በሰጡት ውሳኔ ላይ አስገዳጅ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሰጠ በመሆኑ፤ አሁን ለተያዘው ጉዳይ ይኸው ውሳኔ ተፈፃሚ እንዲደረግ  ሲል ጉባዔው የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲቀርብ ወስኗል።