የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሐሙስ መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ጉባዔ ቀደም ሲል በዋናና ንዑስ ጉባዔ ደረጃ ውይይት ሲደረግባቸው በቆዩ 100 የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ላይ ውሳኔ እና የውሳኔ ሀሳብ ሰጥቷል።
በዚህም በንዑስ እና በዋና ጉባዔው ሰፊ ጥናትና ማጣራት ከተደረገባቸው የዕለቱ 100 የትርጉም አቤቱታዎች መካከል 97ቱ የሕገ መንግሥት ጥሰት የለባቸውም በማለት እንዲዘጉ የወሰነ ሲሆን 2 መዛግብት ለተጨማሪ ማጣራት በይደር እንዲታለፉ በጉባዔው ተወስኗል።
በሌላ በኩል በዕለቱ በነበረው ጉባዔ አንድ መዝገብ የሕገ መንግሥት ጥሰት አለበት በሚል የውሳኔ ሐሳቡ ለትርጉም ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላክ ተወስኗል። አቤቱታውም የከተማ ቤቶችን እና ድርጅቶችን ከግለሰብ ለመውረስ በወጣው አዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት በመንግሥት የተወረሰን ቤት በሚመለከት ለተጠሪዎች አውራሽ በፍ/ቤት መመለሱ የሕገ መንግሥቱን አንቀፅ 40(1) የጣሰ ነው በሚል የተሰጠ ውሳኔ ነው። አዋጁ በሕግ አውጭ አካሉ የወጣው የግለሰቦችን ቤት የሕዝብ እና የመንግስት ለማድረግ በማሰብ ነው። በዚህም ሕግ አውጭው አካል ባወጣው አዋጅ መሰረት የተወረሰን ንብረት የሥራና ቤት ሚኒስቴር (ሕግ አስፈፃሚ ተቋሙ) የማስመለስ ስልጣን የለውም ተብሏል።
በአዋጅ ቁጥር 47/67 ለሥራና ቤት ሚኒስቴር የተሰጠው አንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 110/89 ለፕራይቬታይዜሽን የተሰጠው ሥልጣን መንግሥት በሕግ አግባብ በአዋጅ የወረሰውን ቤት አንዲያጣሩና አንዲመልሱ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከአዋጁ ውጪ አላግባብ በመንግሥት የተያዙትን ቤቶች እያጣሩ አንዲመልሱ ብቻ ነው የሚል መከራከሪያም ቀርቧል፡፡