ጉባዔው በ26 የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
April 16, 2022
ጉባዔው በ36 ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ በ35ቱ ላይ ውሳኔ አሳለፈ
May 20, 2022
Show all

ጉባዔው በ10 ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ  ረቡዕ ሚያዝያ 12 ቀን 2014 ዓ.ም በ10 ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ 8ቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በማለት የወሰነ ሲሆን 2 ጉዳዮችን ለተጨማሪ ጥናት በይደር እንዲሸጋገሩ ወስኗል።

ለተጨማሪ ጥናት በይደር እንዲሸጋገሩ ከተወሰኑ ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያው የህክምና ሙያ ሥነ ምግባርን የሚመለከት ክርክር ሲሆን በወሊድ ወቅት ስለሞተች እናት የአሟሟት ጉዳይ የህክምና ስህተት ነው ወይስ አይደለም የሚል ፍሬ ሐሳብን የያዘ ነው።  ለሕገ መንግስታዊ ጥያቄው መነሻ የሆነው የጤና ሙያ ስነ-ምግባር በወሰነው የ2ኛው ውሳኔ አመልካቾች በክርክሩ ስላለመሳተፋቸው የፌዴራል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሥነ ሥርኣት ጉድለት የለውም በማለት የሰጠው ውሳኔ የመሰማት መብታቸውን ይጥሳል አይጥስም? የስነ ምግባር ኮሚቴውስ የራሱን ውሳኔ በድጋሚ ማየቱ ከህግ አንፃር አግባብነት አለው የለውም በሚሉትና ሌሎች ተያያዥ ነጥቦች ላይ ላይ ጉባዔው ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ጉባዔው በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ተጨማሪ ማስረጃዎች ተጠናቅረውና ጥናት ተደርጎበት ለቀጣይ ውይይት እንዲቀርብ ወስኗል፡፡

ሁለተኛውና ለተጨማሪ ጥናት በይደር የተሸጋገረው ጉዳይ ደግሞ የፍርድ አፈፃፀምን የሚመለከት ሲሆን በዳውሮ ዞን ማንሳ ወንዝ ላይ የሚገነባን የመስኖ ግንባታ የሚመለከት ነው፡፡ ግንባታውን የሚገነባው አካል በ6 ወራት ጨርሶ ማስረከብ የነበረበት ቢሆንም ያንን ባለማድረጉ ውሉ ተቋርጦ ተጠሪው የሠራቸውን ሥራዎች በገለልተኛ ባለሙያ አስለክቶ ለአመልካች እንዲያስረክብ የተወሰነው ውሳኔ ባለመፈፀሙ ነው። ይንንም በተመለከተ በፍርድ ያልተቋቋመ መብት ለማስፈፀም በንብረት ላይ በፍርድ ቤቶች የሚሰጥ የአፈፃፀም ትዕዛዝ ፍትህ ከማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት አንፃር እንዴት ይታያል?  በፍርድ ያልተቋቋመ መብት ለማስፈፀም በፍርድ ቤቶች በንብረት ላይ የሚሰጥ የአፈፃፀም ትዕዛዝ  በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 40 ከተደነገገው የንብረት መብት አንፃርስ ምን አግባብነት አለው? በሚለው ላይ ጉባዔው ሰፊ ውይይት አድርጎ ጉባዔው በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ተጨማሪ ጥናት ተደርጎበት ለቀጣይ ውይይት እንዲቀርብ ወስኗል፡፡