ጉባዔው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከቀረቡለት 847 አቤቱታዎች 793ቱ ሕገ መንግሥት መብት ጥሰት እንደሌለባቸው ገለፀ
August 3, 2023
አጣሪ ጉባዔው በበጀት ዓመት ዕቅዱ ላይ ውይይት አደረገ።
September 13, 2023
Show all

ጉባዔው በ 86 ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ቀደም ሲል በዋናና በንዑስ ጉባዔ ደረጃ ሲወያይባቸው በቆየባቸው 86 ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ በ84ቱ ላይ ምንም አይነት የሕገ መንግሥት ጥሰት ስላላገኘባቸው የሕገመንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም ብሎ ሲወስን በሁለት ጉዳዮች ላይ ደግሞ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት ለመጨረሻ ውሳኔ  ወደፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላኩ ወስኗል፡፡

የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ካላቸው ሁለት ጉዳዮች ውስጥ የመጀመሪያው በየደ/ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግስት የመስኖ ግንባታ ተቋማት አስተዳደር ኤጀንሲ አመልካችነት በፍርድ አፈፃፀም ላይ የቀረበ አቤቱታ ነው፡፡ አቤቱታውም በተሰጠ ፍርድ መሰረት ተጠሪ የሰራውን ስራ በባለሙያ አሳይቶ ያስረክበኝ የሚል ሲሆን ፍርድ ወይም ውሳኔ ሳይሰጥ በአፈፃፀም መዝገብ ላይ እንደ አዲስ በቀረበ የክፍያ ጥያቄ ላይ አመልካች ገንዘቡን አንዲከፍል ፍርድ ቤቶች የሰጡት የአፈፃፀም ትዕዛዝ ሕገ መንግስቱን የሚጥስ ነው በሚል የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡ 

ጉባዔውም በጉዳዩ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ፍርድ ቤቶች በፍርድ ሊወሰን የሚገባ ጉዳይ ሲቀርብላቸው በግራ ቀኙ ተገቢው ክርክር ተደርጎበት፤ ማስረጃ ቀርቦበት በመደበኛው ክርክር ወቅት ውድቅ የተደረገን የዳኝነት ጥያቄ በፍርድ አፈፃፀም ወቅት አንደ አዲስ መደበኛ ክርክር በፍርድ አፈፃፀም መዝገብ ላይ ያልተፈረደን ፍርድ ማስፈፀም አይችሉም፡፡ ለፍርድ ባለመብት በመደኛ ክርክር ወቅት ተረጋግጦ በፍርድ ያልተቋቋመለትን መብት በፍርድ አፈፃፀም ወቅት ሊያቋቁሙለት አይችሉም፡፡ ይህ የሌላኛውን ወገን ፍትህ የማግኘት በተለይም የመከራከር፤ ማስረጃ የማቅረብና ፍርድ ወይም ውሳኔ የማግኘት መብት የሚጥስ ነው፡፡ አንዲሁም በፍርድ ቤት ፍርድ ወይም ውሳኔ ሳይሰጥ በአፈፃፀም መዝገብ ላይ በሚመሰረት ከህግ ውጪ የሆነ መብት መነሻነት ንብረቱ ለፍርድ አፈፃፀም መዋል የለበትም፤ ይህም በህገ መንግስቱ የተደነገገውን የንብረት መብት የሚጥስ ስለሆነ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሕገ መንግስቱን አንቀፅ 37 (1) እና 40 (1) ን የሚጥስ ስለሆነ ለመጨረሻ ውሳኔ ወደ ኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሸን ምክር ቤት አንዲላክ ወስኗል፡፡  

የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል ያለው ሌላው ጉዳይ የሕብረት ሽርክና ማህበር አባልነት ክርክርን የሚመለከት ሲሆን በአመልካችነት የቀረበው የህብረት ስራ ማህበር ተጠሪዎች የማሕበሩ ሕገ ደንብ ባለማክበራቸው ምክንያት በማሕበሩ ህልውና ላይ ችግር በመፍጠራቸው በማሕበሩ ሕገ ደንብ መሠረት ከማህበር አባልነት ተሰናብተው እያለ የሰበር ሰሚ ችሎቱ የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ሽሮ ተጠሪዎች ወደ ማህበሩ ተመልሰው እንዲገቡ በማለት የሰጠው ውሳኔ የሌሎቹን የአመልካች ማህበር አባላት ሕገ መንግስታዊ የመደራጀት መብት የጣሰ ነው በማለት ያቀረቡት ጥያቄ ነው፡፡ ጉባዔውም በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ተወያይቶ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ተጠሪዎች ከማሕበሩ መሰናበታቸው አግባብነት የለውም ሲል የሰጠው ውሳኔ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሠረት የአመልካቾችን የመደራጀት መብት የሚጥስ በመሆኑ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ለመጨረሻ ውሳኔ ወደ ኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሸን ምክር ቤት አንዲላክ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡