የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ 86 ጉዳዮች ላይ በመወያየት 84 ጉዳዮች የሕገመንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በማለት ሲወስን ሁለት ጉዳዮች ላይ በስፋት በመወያየት የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልጋቸው እምነት በማሳደሩ ጉዳዩ የመደመጥ ሂደት/Hearing / እንዲካሄድበት ወይም ተጠሪ መልስ አንዲሰጡበት ወስኗል፡፡
ጉባዔው የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልጋቸው እምነት ካሳደረባቸው ሁለት ጉዳዮች አንዱ ከመኖሪያ ቤት ክርክር ጋር በተያያዘ የንብረት መብትን የሚመለከት ጉዳይ ሲሆን አመልካች አከራካሪው ቤት የራሳቸው ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ የይዞታ ማረጋገጫ በስማቸው የተመዘገበ ቢሆንም የይዞታ ማረጋገጫ አላቸው፡፡ ይህ የይዞታ ማረጋገጫ ለጊዜው በከተማ መስተዳደሩ በሚገኝ የአመልካች የግል ማህደር ውስጥ በሰነድ ያልተገኘ ማስረጃ ቢሆን ከማዘጋጃ ቤቱ በካዳስተር ተመዝግቦ ያለ ስለመሆኑ ግን ተረጋግጧል፡፡ ተጠሪ ለአመልካች የተሰጠው የይዞታ ማረጋገጨ የተገኘው በተጭበረበረ መንገድ ነው ቢሉም ይህን ማረጋገጥ አልቻሉም፡፡ ተጠሪ በቤቱ ላይ ያላቸው ብቸኛ ማስረጃ በቤቱ መብራት እና ውሃ በስማቸው ማስገባታቸውና ግብር መክፈላቸውን የሚያሳይ ማስረጃ አቅርበዋል፡፡ ጉዳዩ የቀረበለት የመጀመሪያ ፍ/ቤት ጉዳያቸውን በሽማግሌ እንዲጨርሱ ሲወስን ተጠሪ አከራካሪው ይዞታ የአመልካች መሆኑን በሽማግሌዎች ፊት አምነው በቤቱ ረዥም ዓመት ስለኖሩ አመልካች ለተጠሪ 60000 (ስልሳ ሺ) ብር ሰጥቶ ቤቱን አንዲለቁ ወይም በከተማው ውስጥ ሌላ ቤት አንዲሰሩላቸው በሚለው ሃሳብ ብቻ ባለመስማማታቸው እርቁ ሊፈርስ በመቻሉ ፍ/ቤቱ የክርክሩን ሂደትና ማስረጃ በመመርመር ተጠሪ ቤቱን ለአመልካች ሊለቁ ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት ከፍተኛ ፍ/ቤትም ተጠሪ በአከራካሪው ቤት የጣሪያና ግርግዳ የከፈሉበት የተለያዩ ዓመታት የግብር ደረሰኞች እና ውሃና መብራት የከፈሉበት ሰነድ በመያዛቸው ከአመልካች ማስረጃ በተሻለ ይዞታው የተጠሪ መሆኑን አረጋግጠዋል በማለት የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን በመሻር ተጠሪ ቤቱን ለአመልካች ሊለቁ አይገባም በማለት ወስኗል፡፡ ቀጥሎ ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በአብላጫ ድምፅ አያስቀርብም ሲል ሲዘጋው በሰበር አቤቱታ ጉዳዩ የቀረበላቸው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በውሳኔው የተፈፀመ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለም በማለት ዘግተውታል፡
ጉባዔውም አከራካሪውን ይዞታ እና ቤት በተመለከተ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚሰጥ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ የያዘ ሰው ባለይዞታ አንደሚሆን ግምት አንደሚወሰድ የፍ/ብ/ህግ አንቀፅ 1195 ይደነግጋል፡፡ ይህን የህግ ግምት ማፍረስ የሚቻለው ባለይዞታው የይዞታ ማረጋገጫውን ያገኘው በተጭበረበረ መንገድ መሆኑን ማስረዳት አንደሚጠበቅበት ከፍ/ብ/ህግ አንቀፅ 1196 መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አመልካች በአከረካሪው ቤት እና ይዞታ ላይ ያላቸው የይዞታ ማረጋገጫ የወረቀት ሰነድ ለጊዜው ባለመገኘቱ ብቻ ፍርድ ቤቶች በግምት ማስረጃው የተሰጠው መመሪያን ባልተከተለ መንገድ ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ የፍ/ህጉን አንቀፅ 1195 እና 1196ን ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ከመተርጎም የመጣ ነው፡፡ በተለይም የፍ/ህጉን አንቀፅ 1196 በጠባቡ መተርጎም ያለበት እና የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ በካዳስተር ወይም በኮምፑተር ተመዝግቦ መገኘት ከወረቀት ሰነድ ይልቅ ወይም በእኩል ደረጃ ባለይዞታነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ፍርድ ቤቶች ሊቀበሉት የሚገባ ነው፡፡ ስለሆነም ዜጎች በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያላቸውን ሕገ መንግስታዊ መብት በሚያስጠብቅ መልኩ የፍ/ህጉ አንቀፅ 1195 እና 1196 መተርጎም አለበት በሚል ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው እምነት በማሳደሩ የመደመጥ ሂደት/Hearing / እንዲካሄድበት ወስኗል፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ ከጥብቅና አገልግሎት ክፍያ ጋር የተያያዘ ሲሆን አመልካቾች ከጠተሪ ጋር ባደረጉት የውል ስምምነት ተጠሪ ማግኘት የሚገባቸውን ንብረት እንዲያገኙ ከወረዳ እስከ ክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ መወከል የጥብቅና አገልግሎት የሰጡና በመጨረሻም ተጠሪ ጉዳያቸውን በስምምነት በመጨረስ ከአከራካሪው ንብረት የራሳቸውንና የልጆቻቸው በወራሽነት የሚያገኙትን ድርሻ ያገኙ ቢሆንም በውል ስምምነቱ መሰረት ክፍያውን አልፈፅምም በማለታቸው እንዲከፍሏቸው የጠየቁ ሲሆን ተጠሪ በበኩላቸው በተለያየ ጊዜ በቀጠሮ ላይ በተደጋጋሚ ቀርተው ጉዳት ከማድረሳቸው ሌላ ጉዳዩን የፈፀምኩት በእርቅ ስለሆነ በስምምነቱ መሰረት ገንዘቡን ልከፍል የሚገባው ጉዳዩ በፍርድ የመጨረሻ ውሳኔ ሲያገኝ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩ የቀረበለት ከፍተኛ ፍ/ቤትም ግራቀኙን በማከራከር አመልካቾች የገቡትን ግዴታ የፈፀሙ ስለሆነ በስምምነቱ መሰረት ተጠሪ ክፍያውን እንዲፈፅሙ ሲወስን በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ የቀረበለት የክልል ጠቅ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አያስቀርብም ሲል መዝገቡን በትእዛዝ ዘግቷል፡፡ ጉዳዩ እንደገና ለክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቀረበ ሲሆን ተጠሪ በስር ፍ/ቤት ከከፈልኩም በተጠሪዎች ግምት መጠን ሳይሆን በነበረው ክርክር ላይ ያገኘሁትን ጥቅም በፍ/ቤት አስገምቶ በሚቀርበው ውጤት ላይ መሆን አለበት እያሉ የቀረበውን ተቃውሞ ወደ ጎን በመተው የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበትና ሊስተካከል የሚገባ ነው ሲል በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 348 መሰረት የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ በመሻር ወስኗል፡፡ አመልካቾች በዚህ ውሳኔ ላይ ያላቸውን አቤቱታ ለፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ችሎቱ ለሰበር አያስቀርብም በማለት ዘግቶታል፡፡
ጉባዔውም በጉዳዩ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ በአጠቃላይ የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት እና የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቶች የሰጡት ውሳኔ አመልካቾች በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 41 እና 33(2) የተሰጣቸውን በመረጡት የስራ ዘርፍ ወይም ሙያ የመሰማራትና ከስራቸው የመጠቀም መብት፣ እንዲሁም በዜግነታቸው ህግ ሊያስገኝላቸው የሚገባውን ጥበቃና ጥቅም የማግኘት መብት የጣሰ ነው በሚል ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው እምነት በማሳደሩ የመደመጥ ሂደት/Hearing / እንዲካሄድበት ወስኗል፡፡