አጣሪ ጉባዔው በ126 የትርጉም አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ሰጠ።
October 30, 2023
ጉባዔው በስድስት የአቤቱታ መዛግብት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
November 17, 2023
Show all

ጉባዔው በሁለት የአቤቱታ መዛግብት ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት ውሳኔ አሳለፈ።

????????????????????????????????????

የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሐሙስ ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በ124 የሕገ መንግሥት የትርጉም አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እና የውሳኔ ሐሳብ ሰጥቷል።

በዕለቱም ጉባዔው በባለሙያዎች እና በንዑስ አጣሪ ጉባዔ  ደረጃ አስፈላጊ ጥናት እና ምርምር ተደርጎባቸው ከቀረቡለት 124 አቤቱታዎች መካከል 118ቱ የሕገ መንግሥት ጥሰት አልተፈፀመባቸውም በሚል እንዲዘጉ የወሰነ ሲሆን ሌሎች ሶስት የአቤቱታ መዛግብት ላይ ተጨማሪ ማጣራት ተደርጎባቸው ለቀጣይ እንዲቀርቡ ተወስኗል።

ከዚህ በተጨማሪም በአመልካች እና በተጠሪ መካከል በተደረሰ ስምምነት አንድ የአቤቱታ መዝገብ ተቋርጦ እንዲዘጋ ተወስኗል። በሌላ በኩል ጉባዔው የሕገ መንግሥት ጥሰት ተፈፅሞባቸዋል በሚል በሁለት የትርጉም አቤቱታዎች ላይ ለፌዴሬሽን ም/ቤት የውሳኔ ሐሳብ እንዲላክ ወስኗል።

የመጀመሪያው ጉዳይም የቤት ሽያጭ ውል ይፍረስልን ክርክርን የሚመለከት ሲሆን፤ ለክርክሩ ምክንያት የሆነው የቤት ሽያጭ ውሉ የተደረገው የውክልና ስልጣን መሻሪያ ውል በሃገር ውስጥ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት የተረጋገጠበትና የተመዘገበበት ጊዜ ከሽያጭ ውሉ በኃላ በመሆኑ ነው።  ለሕገ መንግሥት ትርጉም የቀረበው የፍ/ቤቶች ውሳኔ በአዋጅ ቁጥር 922/2008 ላይ የተቀመጠውን “የውክልና ሰነድ በሃገር ውስጥ ተረጋግጦ ካልተመዘገበ በስተቀር ሕጋዊ ውጤት እንደማይኖረው የሚያስገድደውን የሕጉን ድንጋጌ ወደ ጎን በመተው ሰኔ 17፤18፤20 ቀን 2008 ዓ/ም በአሜሪካን ሀገር የተረጋገጠና በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ደግሞ ሃምሌ 12 ቀን 2008 ዓ/ም ተረጋግጦና ተመዝግቦ ወደ ሕጋዊ ውጤት የገባውን የውክልና መሻሪያ ሰነድ በአዋጁ የማረጋገጥና የመመዝገብ ሥልጣን የተሰጣቸው ተቋማት ባላረጋገጡበት እና ባልመዘገቡበት ሰኔ 11 ቀን 2008 ዓ/ም “ውክልናው እንደተሻረ ይቆጠራል” በሚል መወሰኑ የሕጉ ድንጋጌ ሕገ መንግሥቱን በሚቃረን መልኩ መተርጎሙን ያመለክታል ተብሏል፡፡

አመልካቾች ለክርክሩ መነሻ በሆነው ንብረት ላይ በገንዘባቸው በግዥ ውል ስምምነት ንብረቱን ለመሸጥ የውክልና ስልጣን ካለው እና የውክልና ስልጣኑ ካልተሻረው ተጠሪ ጋር ባደረጉት ውል የንብረቱ ባለቤት ሆነዋል፡፡ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40(1) መሰረት “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ ይከበርለታል። ይህ መብት ለሕዝብ ጥቅም በሕግ እስካልተወሰነ ድረስ ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም፤ የመሸጥ፣ የማውረስ፣ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል” በማለት ደንግጓል፡፡ “ንብረት ማለት ደግሞ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በጉልበቱ፣ በመፍጠር ችሎታው ወይም በካፒታሉ ያፈራው ተጨባጭ የሆነና የተጨባጭነት ዋጋ ያለው ውጤት ነው” በማለት የሚደነግገውን ሕገ መንግሥትዊ መብታቸውን በመጣስ የውክልና ስልጣን ያልተሻረበትንና ያልተረጋገጠበትን ጊዜ በማስረጃነት በመውሰድ የተሰጠው ውሳኔ የአመልካቾችን ንብረት የማፍራት መብት የሚጻረር ውሳኔ ነው፡፡ አመልካቾችም በዚህ ንብረት ላይ የመሰረቱትን መብት በሕጋዊ መንገድ ባላጡበት ሁኔታ በፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 40(1) ድንጋጌ የሚቃረን በመሆኑ በውሳኔው ላይ የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በሚል ለመጨረሻ ውሳኔ ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላክ ተወስኗል።

2ኛው እና በዕለቱ  ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት ለመጨረሻ ውሳኔ እንዲላክ በጉባዔው የተወሰነው ጉዳይ ደግሞ ሁከት ይወገድልኝ ጥያቄን መሰረት አድርጎ የመንግሥት መሬትን የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ጥያቄን የሚመለከት ነው፡፡ ጉዳዩም በቀበሌ አስተዳደር እና ም/ቤት ውሳኔ የተሰጠን የገጠር የይዞታ መሬት በዞን እና በወረዳ በተዋረድ በመጣ የፍትሃዊነት እና የተገቢነት ጥያቄ እንዲታገድ መወሰኑ ሁከት ሊባል ይችላል ወይስ አይችልም የሚል ጉዳይን ይመለከታል።

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 40 (3) መሰረት “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው” በማለት ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 40 (4) ደግሞ “የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው፡፡” አፈፃፀሙን በተመለከተ ዝርዝር ሕግ ይወጣል በማለት ይደነግጋል፡፡

በዚህ ክርክር ተጠሪዎች በቀበሌ አስተዳደር እና ም/ቤት ውሳኔ መሬት በተቀበሉ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የመሬት ሽንሸናው “አድሎአዊ እና ሕግን ያልተከተለ ነው” በሚል የእግድ ትዕዛዙ ከዞንና ከወረዳ መፃፉንና መሬቱ ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲሆን መታዘዙ መሬቱ በተጠሪዎች እጅ ያልገባ እና በይዞታ መልኩ ልማት ያልተለማበት መሆኑ እንዲሁም የዕግድ ደብዳቤውን የፃፉ የመንግሥት አካላት (የአሁን አመልካቾች) በሕግ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት የገጠር መሬት ለማን በነፃ መሰጠት እንዳለበት የመወሰን፤ የመሬት ሽንሸና ሂደቱ ሕጉን የጠበቀ መሆን አለመሆኑን የማረጋገጥ፤ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው አግባብ ከአድሎ በፀዳና በግልፀኝነት የተፈፀመ መሆን አለመሆኑን የመመርመርና ሕገ ወጥ የሆነ ድርጊት ሲኖር የእርምት እርምጃ የመውሰድ በተጨማሪም ሽንሸናውን ለጊዜውም የማስቆም ስልጣን አላቸው፡፡ ይህም ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነትን መወጣት እንጅ ሁከት መፍጠር ሊባል አይችልም ተብሏል። በመሆኑም ፍ/ቤቶቹ የሰጡት ውሳኔ የሕገ መንግሥቱን አንቀፅ 40(3) እና 52(2)መ ን የሚጥስ በመሆኑ ለመጨረሻ ውሳኔ ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላክ ተወስኗል።

ከዚህ ጉዳይ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ እና በጉባዔው ሬጅስትራር የተከፈቱ መዝገቦች ላይ ባሉ ጉዳዮች ላይ ይህ የውሳኔ ሃሳብ ተፈፃሚ አንዲሆን ሲል ጉባዔው ውሳኔ ሰጥቷል።