ጉባዔው በአንድ ሕገ መንግስታዊ ጉዳይ ላይ የውሳኔ ሀሳብ አሳለፈ
February 17, 2021

ጉባዔው በሁለት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሀሳብ አሳለፈ

ጉባዔው በሁለት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሀሳብ አሳለፈ

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ 20 ጉዳዮች ላይ በመወያየት 18 ጉዳዮችን የሕገ መንግስት ትርጉም አያስፈልጋቸውም ብሎ ውሳኔ በመስጠት የዘጋቸው ሲሆን  በሁለት  ጉዳዮች ላይ  የውሳኔ ሀሳብ በማሳለፍ ለመጨረሻ ውሳኔ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲላክ ወስኗል፡፡

ጉባዔው ከመረመራቸው 20 ጉዳዮች ውስጥ የውሳኔ ሀሳብ የቀረበበት የመጀመሪያው ጉዳይ የገጠር መሬትን የሚመለከት ሲሆን አመልካች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሴት አርሶ አደር እና የሟች የቤተሰብ አባል የነበሩ መሆኑ እያታወቀ አግብተው በመሄዳቸው ብቻ ከቤተሰብ አባልነት ውጪ ናቸው በማለት ከውርስ ውጪ እንዲሆኑ በፍርድ ቤቶች የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም የቀረበ ሕገ መንግሥታዊ ክርክርን የሚመለከት ነው፡፡

               ጉዳዩ አመልካች የሟች አያታቸው የቤተሰብ አባል የነበሩና ከሟች ይዞታ በሚገኝ ገቢ ይተዳደሩ እንደነበርና ትዳራቸው ከፈረሰም በኋላ ሌላ መተዳደሪያ ስለሌላቸው ተመልሰው ከሟች ይዞታ ገቢ በመጋራት ይተዳደሩ እንደነበር ሳያረጋግጥ ባል አግብተው ስለሄዱ ብቻ ከቤተሰብ አባልነት አስተዳደር ውጪ ሆነዋል በማለት የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የደረሰበት ድምዳሜ አብዛኛውን የአርሶ አደር ሴቶች የትዳር ሁኔታን ያላገናዘበና ሕገ መንግሥቱ በአንቀፅ 34/1 እና 35/7 ለሴቶችና ለጋብቻ ያስቀመጠውን መብት የሚጥስ በመሆኑ ለመጨረሻ የሕገ መንግሥት ትርጉም ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላክ የውሳኔ ሀሳቡን አቅርቧል፡፡

 ሁለተኛው ጉዳይ የከተማ ቦታ ምትክ መሬትና የካሳ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን አመልካች በሕጉ መሰረት ምትክ ቦታና ተገቢው ካሳ ሳይሰጣቸው በደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ ሊች አምባ ቀበሌ የሚገኘውን የግል ይዞታቸውን በልማት ምክንያት መንግስት ወስዶብኛል በሚል ተከራክረው ፍትሕ አለማግኘታቸውን በመቃወም የቀረበ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 40(8) መሰረት በልማት ምክንያት ከግለሰቦች የሚወሰዱ ይዞታዎችን በሚመለከት መሬቱን የሚወስደው የክልል ወይም የፌዴራል መንግስት የበላይ አካል በቅድሚያ ካሳ እንዲከፈል በማድረግ መሬቱን ማስለቀቅ እንዳለበት የተደነገገ ቢሆንም አመልካች ለረዥም ጊዜ ምትክ ቦታና ካሳ አንዲከፈላቸው ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ፍርድ ቤቶቹ ለአመልካች የካሳ ግምት እንደተሰራላቸው በመቁጠር ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለንም በማለት የአመልካችን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ  አላግባብ ለረጅም ጊዜ የፍርድ ቤት ክርክር እንዲያደርጉ ማድረጉ የአመልካችን ፍትህ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የጣሰ በመሆኑ ለመጨረሻ የሕገ መንግሥት ትርጉም ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላክ የውሳኔ ሀሳቡን አቅርቧል፡፡