የክልል የፍትህ አካላትን ማጠናከር ለዜጎች የተፋጠነ ፍትህን ለመስጠት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ
January 22, 2020
በጉባዔው ም/ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሠለሞን አረዳ የተመራው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ልዑካን ቡድን ጀርመን በርሊን የልምድ ልውውጥ አካሄደ
February 14, 2020

ጉባዔው ሁለት መዝገቦችን ለሕገ መንግሥት ትርጉም ወደ ፌ/ም/ቤት ላከ

ጉባዔው ሁለት መዝገቦችን ለሕገ መንግሥት ትርጉም ወደ ፌ/ም/ቤት ላከ

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በዛሬ የካቲት 05/2012 ውሎው ከመረመራቸው 27 ጉዳዮች ውስጥ ሁለቱን ለሕገ መንግሥት ትርጉም ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲላኩ ወስኗል።

ጉባዔው ዛሬ ባከናወነው የባለጉዳዮችን መዝገብ የማጣራት መደበኛ ስብሰባው 27 መዝገቦችን የመረመረ ሲሆን፣ ከመረመራቸው መዝገቦች መካከል ሁለቱ ጉዳዮች ላይ የሕገ መንግሥት ጥሰት ተገኝቶባቸዋል ብሎ በማመኑ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትርጉም እንዲላኩ የውሳኔ ሀሳብ አሳልፏል። ቀሪዎቹ 25 መዝገቦች የሕገ መንግሥት ትርጉም የማያስፈልጋቸው በመሆኑ ውሳኔ በመስጠት ዘግቷቸዋል።

ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ለትርጉም የውሳኔ ሀሳብ የቀረበበት አንዱ ጉዳይ ከመንግሥታዊ ተቋም የቀረበ ሲሆን፣ ጉዳዩም በመንግስታዊ ተቋም የሚሰሩ የቀን ሰራተኞች የስራ ክርክር ሂደትን በተመለከተ የሚዳኝ ህግ ዙርያ የፌደራል የሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ሕገ መንግስታዊነት የተመለከተ ነው፡፡ ጉዳዩ ከአማራ ክልል የመጣ ሲሆን ከወረዳ ፍርድ ቤት ጀምሮ ሲታይ ቆይቶ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ውሳኔ ከተሰጠው  በኋላ አመልካች የሆነው የመንግስት ተቋም በፍ/ቤቶቹ ውሳኔ ቅር በመሰኘትና ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ተጥሷል በማለት ለጉባዔው የቀረበ ነው። ጉባዔውም የቀረበውን ጉዳይ ከሕገ መንግሥቱ አንጻር ካጣራ በኋላ የፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ ከተደነገጉት አንቀፆች መካከል አንቀፅ 55 ንዑስ 1 እና 3 እንዲሁም አንቀፅ 79 ንዑስ አንቀፅ 3 ጋር ይቃረናል ብሎ በማመኑ ለመጨረሻ ውሳኔና ለሕገ መንግሥት ትርጉም ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲላክ የውሳኔ ሀሳብ አሳልፏል።

ሁለተኛው መዝገብ በግለሰቦች መካከል ከውል ጋር በተያያዘ የሚደረጉ የግልግል ዳኝነቶችን በተመለከተ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠው ውሳኔ ፍትህ ከማግኘት መብት አንፃር በሚል የታየ ነው፡፡ ክርክሩም ባለጉዳዩ ግለሰብ ሕገ መንግሥታዊ መብቴ በፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ ስለተጣሰብኝ ትርጉም ይሰጥልኝ በማለት ለጉባዔው ያቀረበው ነው። ጉባዔውም በተመሳሳይ ጉዳዩን ከሕገ መንግሥቱ አንጻር ካጣራ በኋላ የፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገ መብት ጋር ማለትም በአንቀፅ 37 ከተቀመጠው ፍትህ የማግኘት መብት ጋር ይቃረናል ብሎ ስላመነ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት የውሳኔ ሀሳቡን አሳልፏል።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመ ሕገ መንግሥታዊ፣ ነፃና ገለልተኛ ተቋም ሲሆን፣ ከተለያዩ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና የመንግስት አካላት የሚቀርቡለትን የሕገ መንግሥት ይጣራልኝ ጉዳዮች በመቀበል ከሕገ መንግሥቱ አንጻር በመመርመር ትርጉም የሚያስፈልጋቸውን ለመጨረሻ ውሳኔ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲልክ፣ ትርጉም የማያስፈልጋቸውን ደግሞ ውሳኔ በመስጠት ለአቤቱታ አቅራቢው የሚያሳውቅ ተቋም ነው።