የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እስካሁን ላከናወናቸው ተግባራት ታላቅ ክብርና ምሥጋና እንዳላቸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩⵆ
January 20, 2022
በአዲስ አባላት የተዋቀረው ጉባዔ የመጀመሪያ ውይይቱን አደረገ
February 21, 2022

የጉባዔው የቀድሞ አባላት አዲስ ለተሾሙ የጉባዔ አባላት ልምዳቸውን አካፈሉ

????????????????????????????????????

ጥር 09/2014 በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላት በጉባዔው በቆዩባቸው ጊዜያት የነበራቸውን ልምድ አዲስ ለተሾሙት የጉባዔ አባላት አካፈሉ።

የሕገ መንግት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ም/ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሰሎሞን አረዳ የቀድሞ የጉባዔ አባላት በሕገ መንግስት ትርጉም ስርዓት ውስጥ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበው በነበረው የትርጉም ሂደት ውስጥ ከእያንዳንዱ የጉባዔ አባል የተወሰደ የራሱ የሆነ ትልቅ ትምህርት መኖሩን አውስተዋል፡፡

በልምድ ማካፈል የምክክር መድረኩ ላይ ለሁለት ዙር ማለትም ለ12 ዓመታት ያህል ያገለገሉት ክቡር አቶ ሚሊዮን አሰፋ በስራ ውስጥ ስላሳለፉት ተሞክሮ ሰፋ ያለ ገለፃ አድርገዋል። በገለፃቸውም የጉባዔው ተግባር ትልቅ መሆኑን አውስተው፣ በሕዝብ የተመረጠ አካል ያወጣውን ሕግ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ብሎ የውሳኔ ሀሳብ የማቅረብ ሥልጣን ያለው ተቋም መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጉባዔው በሚያደርገው ማጣራት ማንኛውም ሕግ ወይም የባለሥልጣን ውሳኔን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ሆኖ ሲያገኘው እንዲሻር በመጠየቅ የማሻር ሥልጣን ያለው ተቋም በመሆኑ የጉባዔውን ተግባር የላቀና ሕገ መንግሥታዊነት እንዲረጋገጥ የሚኖረውንም ድርሻ የጎላ ያደርገዋል ብለዋል።

አቶ ሚሊዮን በጉባዔው በቆዩባቸው ረጅም ዓመታት ያገኟቸውን መልካም ዕድሎች በማንሳት ለአዲሶቹ ተሿሚዎች ገልፀው፣ ጉባዔው የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ሙያዊ ውይይት ውስጥ ትልቅ የዕውቀት ማግኛ መድረክ ሆኖም እንደሚያገልግል በመግለፅ ከዚህ አንፃር ያላቸውን በርካታ ልምዶቻቸውን አቅርበዋል።

በጉባዔው ጽ/ቤት የሕገ መንግሥት አስተምሮና ስርፀት የቡድን መሪ የሆኑት አቶ ያደታ ግዛውም የሕገ መንግሥትን ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ታሪካዊ ዳራ፣ የጉባዔውን ሥልጣን፣ ተግባርና አወቃቀር እንዲሁም የሕገ መንግሥታዊ አቤቱታ አቀራረብን የተመለከቱ ጉዳዮችን የያዘ የውይይት መነሻ የሚሆን ፅሑፍ አቅርበዋል።

ሌሎች የቀድሞ የጉባዔው አባላትም የጉዳዮቻቸውን የመጨረሻ ውሳኔ በተስፋ የሚጠብቁ በርካታ አቤቱታ አቅራቢዎች ያሉ በመሆናቸው አዲስ የተሾሙ የጉባዔው አባላት በከፍተኛ ሀላፊነት ጊዜና ሙሉ አቅማቸውን ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም የሚሰጠው ትርጉም የሚያመጣውን ውጤት አስቀድሞ በመገምገምና ለሀገርና ለህብረተሰብ የሚያመጣውን ፋይዳ በመመዘን ላይ በማተኮር መስራት እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡ ፅ/ቤቱ ጥሩ አቅም ያላቸው ባለሙያዎች ቢኖሩትም የተሻለ ሰፋ ያለ አቅም ለመፍጠር ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስራ መስራት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

በቀረበው ፅሑፍ እና አጠቃላይ በቀረቡ ገለፃዎች ላይም ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ አዲስ ተሿሚዎችም በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን በመግለፅ የቀረበላቸው መረጃ ለቀጣይ ሥራቸው አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

በመጨረሻም የንዑስ ጉባዔ አባላት ምርጫ ተከናውኖ እና የንዑስና የዋና ጉባዔ የስብሰባ ቀናት ተወስነው ውይይቱ ተጠናቋል።