ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕገ መንግስታዊ ፍ/ቤቶችና መሰል ተቋማት ስራ አስፈፃሚ ቢሮ አባል ሆና ተመረጠች
July 2, 2019
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች እና ለልማት ተነሺዎች ለማስተላለፍ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2008 አንቀጽ 44 (ሐ) እና (ሠ) የሕገ መንግስቱን አንቀፅ 40 ድንጋጌዎች የሚቃረን መሆኑ ተገለፀ
July 12, 2019

የዓለም አቀፉ ሕገ መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች ዋና ጸሀፊ ኢትዮጵያን ጎበኙ

 

የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሰኔ 7 ቀን 2011 ዓ.ም  ወደ አዲስ አበባ የገቡትን የአለም አቀፍ የሕገ መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች /World Conference of Constitutional Jurisdiction (WCCJ)/  ዋና ጸሀፊ ሚ/ር ሺኑትዝ ዱር አቀባበል አደረገላቸው።

የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሰብሳቢ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ እና የጉባኤው አባላት ለዋና ጸሀፊ ሚ/ር ሺኑትዝ ዱር ወደ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጡ የሚል መልዕክት አስተላልፈው፣ የዛሬው ጉብኝት የሁለቱን ተቋማት ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድገው መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ አባል ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ከአለም አቀፍ የሕገ መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች ተቋም ጋር የተሻለ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን በቀጣይም ይህን አጋርነት በከፍተኛ ደረጃ ማጠናከር እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ተመልክቷል፡፡

ለዋና ጸሀፊ ሚ/ር ሺኑትዝ ዱር ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና ስለ ጉባኤው አሰራርና አደረጃጀት ገለጻ ያደረጉት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባል ዶ/ር ፋሲል ናሆም፣ የሁለቱ ተቋማት ግንኙነት መጠናከር ሕገ መንግስታዊ አተረጓጎም ላይ የተሻለ አረዳድ እንዲኖርና የሕገ መንግስት ሉዓላዊነት እንዲሰፍን እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በለውጥ ላይ ያለች አገር መሆኗን ጠቅሰው በተለይ ከሁሉም ጎረቤት አገሮች ጋር ሰላም በመፍጠር በኃይል የሚንቀሳቀሱ ተቀዋሚ ቡድኖች ወደ አገራቸው በሰላም እንዲገቡ መደረጉ በአገሪቷ ሰላም እንዲሰፍን እና ሁሉም ዜጎች በአገራቸው ፖለቲካ ላይ እንዲሳተፉ መደረጉን አመልክተዋል።

ሕገ መንግስቱ የጾታ እኩልነትን በተገቢው መንገድ የሚያንጸባርቅ ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት በመንግስት ስልጣን ላይ ሴቶች ተሳታፊ አለመሆናቸውን ጠቅሰው በአሁኑ ጊዜ ሃምሳ በመቶ የአስፈጻሚውን ስልጣን መያዛቸውን አስረድተዋል። የሕገ መንግስት ማሻሻያ ሀሳብ ከተለያ ወገኖች እየቀረበ መሆኑንና በቀጣይ ምርጫ በኋላ የህገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ መንግስት ጥናት እያደረገ እንደሆነም ዶ/ር ፋሲል ተናግረዋል።

የጉባኤው ስልጣንና ተግባር ምን እንደሚመስል የተብራራ ሲሆን፣ በተለይ ከፌዴሬሽን ም/ቤት ጋር ያለውን ግንኙነት አስረድተው ሚ/ር ሺኑትዝ ዱር በኢትዮጵያ መልካም ቆይታ እንዲኖራቸው ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ዋና ጸሀፊ ሚ/ር ሺኑትዝ ዱር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውና ሁለቱ ተቋማት አሁን ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ለቀጣይ በሕገ መንግስት አተረጓጎም ዙሪያ የተሻለ ልምድ መለዋወጥ እንዳለባቸው አመልክተው፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በዶ/ር ፋሲልም ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል። ዋና ጸሀፊው በአዲስ አበባ በነበራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ በከተማዋ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችንም ጎብኝተዋል።