የክብርት ሰብሳቢዋ መልክት

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተጎናፀፉትን ነፃነትና በመፈቃቀድ ላይ የመሠረቱትን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማጠናከርና የፈጠሩትን ፌዴራላዊ ሥርዓት በጋራ ለመንከባከብ ቃል የገቡበትን ሕገመንግሥት ለመተርጐም ሥልጣን ለተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሙያዊ እገዛ ለማድረግ በሕገመንግሥቱ ተቋቁሞ፣ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሕገመንግሥት ትርጉም ማጣራት ተግባርን በማከናወን ላይ የሚገኝ ተቋም ነው። ይህንንም ኃላፊነቱን ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ ግለሰቦች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚቀርቡ የሕገመንግሥት ትርጉም ጥያቄዎችን በማጣራት  ሲከናውን ቆይቷል።

ጉባዔው በሕገመንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 798/2005 ዓ.ም የተሰጡትን ኃላፊነቶች ከወትሮው በተሻለ የአፈፃፀም ብቃትና አድማስ ለመፈፀም ለሚቀጥሉት ጊዜያት ትኩረት የምንሰጥባቸውን መስኮች መለየት ተችሏል። የጉባዔውን የአፈፃፀም ብቃት ቀደም ሲል ከነበረው የተሻለ በማድረግ፣ ሕገመንግሥታዊነትን በጥልቀት አስርፆ አንድ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ በመገንባት ሂደት የሚኖረንን ወሳኝ ሚና ከግብ ለማድረስ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን።

መልካም አጋጣሚዎችን አሟጦ ለመጠቀምና ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና ሲከሰቱም ፈጣን የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ሥራዎቻችንን ሁሉ በተደራጀ ዕቅድ መምራት እንደሚኖርብን በማመን ይህንኑ በመድረግ ላይ እንገኛለን። በሕገመንግሥቱ የተጣለብን ኃላፊነት በሚገባ መወጣት ከቻልን አመርቂ ውጤት ማስመዝገብና የኅብረተሰቡንም የፍትህ ጥማት ማርካት እንደምንችል ከወዲሁ ያለኝን እምነት እየገለጽኩ፣ የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላት፣ የጽ/ቤቱ አመራርና ባለሙያዎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ
የጉባዔው ሰብሳቢ