ከሕገ መንግስት አተረጓጎም ጋር ተያይዞ በተጠኑ ጉዳዮች ላይ ከአማራብ/ክ/መ ክልል ዳኞች ጋር ውይይት ተደረገ
December 31, 2019
ጉባዔው ሁለት መዝገቦችን ለሕገ መንግሥት ትርጉም ወደ ፌ/ም/ቤት ላከ
February 13, 2020

የክልል የፍትህ አካላትን ማጠናከር ለዜጎች የተፋጠነ ፍትህን ለመስጠት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

የክልል የፍትህ አካላትን ማጠናከር ለዜጎች የተፋጠነ ፍትህን ለመስጠት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጥር 9 እና 10/2012 ዓ.ም በደቡብ ክልል አርባምንጭ ከተማ ከሕገ መንግሥት አተረጓጎም ጋር ተያይዞ በተጠኑ ጉዳዮች ላይ ከደቡብ ብ/ብ/ህ/ብ/ክ/መ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኞች እና ከክልሉ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላት ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

በውይይት መድረኩ “የሕገ መንግሥት ትርጉም መርሆዎች”፣ “የገጠር መሬት ስለሚተላለፍበት አግባብ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት አንፃር”፣ “የአስተዳደር ፍ/ቤት ውሳኔዎች በመደበኛ ፍ/ቤት እንዳይታይ የሚከለክሉ ሕጎች ሕገ መንግሥታዊነት”፣ እና “ከፍርድ ቤት የሚላኩ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎች ምንነትና አተገባበር” የሚሉ ሦስት ፅሑፎች በጉባዔው ልዩ ረዳት አቶ ከበበውና በጉባዔው ጽ/ቤት ባለሙያዎች የቀረቡ ሲሆን፤ በተጨማሪም “የደቡብ ክልል አጣሪ ጉባዔ አወቃቀርና እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራትን” የተመለከተ ፅሑፍም በክልሉ አጣሪ ጉባዔ ጽ/ቤት የቴክኒክ ቡድን አባል በአቶ ሉቃስ ግርማ ቀርቧል፡፡

በቀረቡት ፅሁፎች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተስጥቷቸዋል። የክልል የፍትህ ተቋማትን የሕግ መንግሥት አጣሪ ጉባዔውን ጨምሮ መጠናከር እንዳለባቸው ሀሳብ የቀረበ ሲሆን፣ ለዚህም የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት እገዛ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል፡፡ ክልል ላይ ያሉት ተቋማት በተጠናከሩ ቁጥር የዜጎች የፍትህ ጥያቄ በዛው ልክ ምላሽ እንደሚያገኝና ወደ ፌዴራሉ የሚመጣውንም ጫና እና የዜጎች እንግልትን የሚቀንስ መሆኑም ተነስቷል፡፡

የደቡብ ክልል የብሔር ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ክቡር አቶ ለማ ጉዝሜ በበኩላቸው ሕገ መንግሥት ሳይተረጉም የሚሠራ የፍትህ አካል የሌለ መሆኑን ጠቁመው የሕገ መንግሥት አተረጓጎም ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቀት መያዝ ለትርጉም ሥራዎች መቃናት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሕገ መንግሥት የሁላችንም ሰነድ ከመሆኑ አንጻር በአሠራር የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ሕገ መንግሥቱን በማክበርና በማስከበር ረገድ ለአተረጓጎም ትልቅ ዋጋ መሰጠት እንዳለበት ገልፀው፣ እንደ ሀገርም የሚፈጠሩ ቀውሶችን በመፍታት ሰላምን ለማስፈን የሕገ መንግሥቱን መርህ በመጠበቅ መሥራት አንደሚገባ ተናግረዋል፡፡