አጣሪ ጉባዔው 41 ጉዳዮችን በመመርመር የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በማለት ውሳኔ አሳለፈ
June 10, 2022
የመንግሥት ሠራተኛን በኃላፊ በተፃፈ ደብዳቤ ብቻ ከሥራ ማሰናበትሕገ መንግሥታዊ ነውን?
June 20, 2022

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፌዴሬሽን ም/ቤትና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላት በሕገ መንግሥት ትርጉም ዙርያ የጋራ የምክክር አደረጉ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፌዴሬሽን ም/ቤትና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላት ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ የሕገ መንግሥት ትርጉም አሰጣጥ ሂደትን አስመልክቶ የጋራ የምክክር አደረጉ፡፡

የምክክር መድረኩን በይፋ የከፈቱት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፌዴሬሽን ም/ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ የተከበሩ ወ/ሮ ዛህራ ሑመድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሚቀርቡለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም የውሳኔ ሐሳቦችን ተቀብሎ በመመርመር 90 በመቶውን የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዳፀደቀ ገልፀዋል፡፡ አክለውም የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በሕገ መንግስሥቱ የተሰጣቸውን ሕገ መንግሥታዊ ተልእኮ በብቃትና በውጤታማነት መፈጸም እንዲችሉ በየጊዜው እየተገናኙ ለመመካከርና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችም ካሉ በጋራ በመነጋገር መፍትሄ ለመስጠት እንዲህ አይነት የምክክር መድረክ መዘጋጀቱ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

በፌዴሬሽን ም/ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉምና ውሳኔ አፈፃፀም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ ፀሀፊ የተከበሩ ወ/ሮ ፀሀይ ወራሳ በበኩላቸው የሕገ መንግስት ትርጉም መስጠት የፌዴሬሽም ም/ቤት የመጀመሪያ ተግባር እንደሆነና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔም ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር ወይም የመንግስት አካል ወይም የባለስልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረንና ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሃሳብ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ሲያቀርብ ትርጉም የማያስፈልገው ሆኖ ባገኘው ጊዜ ደግሞ ትርጉም አያስፈልገውም የሚል ውሳኔ እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡ በውይይቱም በሕገ መንግሥት ትርጉም የአሰራር ስርአት ላይ ግንዛቤ መፍጠርና በአሰራር ሂደቶች ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶች ላይ የጋራ ምክክር በማድረግ የተሻለ ቅንጅት ለመፍጠርና ለሚያጋጥሙ ችግሮችም የተደራጀና የተቀናጀ አማራጭ የመፍትሔ ሃሳብ በማሰባሰብ በሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔዎች ላይ የላቀ የአፈጻጸም ውጤት ለማግኘት ይረዳል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

በእለቱ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አደረጃጀትና አሰራርን የተመለከከተ ፅሁፍ በአጣሪ ጉባዔው የፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ወዬሳ፣ በሕገ መንግሥት ትርጉም የአሰራር ስርአት ላይ እንደተግዳሮት የሚታዩ ጉዳዮችን በተመለከተ በም/ቤቱ ፅ/ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉምና የሕጎች ሕገ መንግሥታዊነት ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት ወ/ሮ ብርቱካን መለሰ እንዲሁም የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታ አቀባበል፣አያያዝና ምላሽ አሰጣጥ መመሪያን በተመለከተ የሕገ መንግሥት ትርጉም ከፍተኛ ባለሙያ በሆኑት በአቶ ሙሉዬ ወለላ አማካኝነት በተከታታይ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በውይይቱም በተለይ የፌዴሬሽን ም/ቤት አዲስ ባወጣው መመሪያ ላይ በርካታ ከግልፅነት፣ ከቃላት አጠቃቀምና ከባለቤትነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን በተከበሩ የምቤቱ ቤቱ ምክትል አፈጉባዔ እንዲሁም የሕገ መንግሥት ትርጉምና ውሳኔ አፈፃፀም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በሆኑት የተከበሩ ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ አወያይነት ሰፋ ያለ ውይይትም ተደርጎበታል፡፡

በመጨረሻም የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባዔ የተከበሩ ወ/ሮ ዛህራ ሑመድ መመሪያው ወደፊት ምክር ቤቱና ጉባዔው በጋራ የሚመሩበትና የሚተገብሩት መመሪያ ከመሆኑ አንፃር ሁለቱም የተስማሙበትና ያመኑበት መሆን ስለሚገባው በቀጣይ የሁለቱም ተቋማት አመራሮች በተገኙበት አንድ መድረክ ተዘጋጅቶ የጋራ መግባባት ሊደረስበት እንደሚገባ አመልክተው የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡