ለቃሊቲ ኮንስትራክሽን ዕቃዎች ማምረቻ ፋብሪካ ሴት ሰራተኞች በሴቶች መብቶች ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
November 20, 2019
ጉባዔው ከሕገ መንግሥት አተረጓጎም ጋር ተያይዞ በተሰጡ ጉዳዮች ላይ ከኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኞች ጋር ተወያየ
December 2, 2019

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አዲስ ሶፍት ዌር ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ተረከበ

????????????????????????????????????

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አዲስ ሶፍት ዌር ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ተረከበ

 

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ለተገልጋዮች ያለውን ተደራሽ የሚያሳድግና የጉዳዮች ፍስት አሰራርን የሚያዘምን የሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዳራሽ ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ጋር የርክክብ ስነ ስርዓት አካሄደ።

በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳዱካን ደበበ ሶፍትዌሩ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አሠራርን ከማዘመን ባሻገር ተገልጋዮች ባሉበት ከተቋሙ ጋር ግንኙነት የሚፈጥሩበት ሁኔታን የሚያመቻች እንደሆነ ጠቁመው ሶፍትዌሩን ወደ ተግባር ማስገባት ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ሲሆን፣ በሥራ ሂደትም የሚከሰቱ ክፍተቶችን  በመለየት አዳዲስ የሚጨመሩ ቴክኖሎጂዎች  የሚካተቱበት እንደሚሆን ገልጸዋል።

ሶፍትዌሩ ሊጎለብት የቻለው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ባቀረበው የግብዓት ጥያቄ መሰረት ሲሆን፣ በቀረበው መሰረትም ዲዛይን ተደርጎ ለዚህ ቀን እንዲበቃ መደረጉ ትልቅ እመርታ እንደሆነ ተናግረው ተቋሙም በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ጥያቄ ማቅረቡ  ሊመሰገን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዬሳ በበኩላቸው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሕገ መንግሥቱ ከተቋቋሙ ተቋማት አንዱ እንደሆነና  በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት ሕገ መንግሥታዊ ጥሰቶችን በማጣራት ዜጎች መብታቸው እንዲጠበቅ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ቢሆንም፣  ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አቤቱታ የሚያቀርቡ አካላት እየተበራከቱ እንደሚገኙና የመዝገብ ድግግሞሽም እየተፈጠረ በመሆኑ ለሶፍትዌሩ መጎልበት አንዱ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም ለእነዚህ ዜጎች ተደራሽ ለመሆንና የመዝገቦች ድግግሞሽን ለማስቀረት  የዘመነ አሠራር መፍጠር ተገቢነት ያለው መሆኑንና ለዚህም ከጉዳዮች ፍሰት ጀምሮ እስከ ጥናትና ምርመር ድረስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር በመፍጠር ተገልጋዮችን የማርካት ሥራ መሠራት እንዳለበት ጠቁመው ኢንስቲትዩቱ ላደረገው እገዛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሶፍትዌሩ ዙሪያ በጥናት ቡድኑ ተወካይ አቶ ሰልማን መሀመድ ገለጻ  ተደርጎ  የተለያዩ  አስተያየቶች ከተሳታፊዎች የተነሳ ሲሆን፣ በመጨረሻም በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በአቶ ሳዱካን ደበበ እና በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽ/ቤት ኃላፊ በአቶ ደሳለኝ ወዬሳ የሶፍትዌሩ ሞጁል ርክክብ ስነ ስርዓት ተከናውኗል።