በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የሕገ መንግሥት አተረጓጎም ሥርዓትን ለማጠናከር የሚያስችል የምክክር መድረክ ተካሄደ
December 31, 2018
የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ልዑካን ቡድን በኮትዲቯር ኮንፍረንስ ላይ ተሳተፈ
February 19, 2019

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀፅ 37 ከሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 37/1/ ጋር የሚጋጭ መሆኑ ተገለጸ

የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ የቀረቡለትን ሰባት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎችን በማጣራት፣ ከቀረቡት ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀፅ 37 ከሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 37/1  ጋር የሚቃረን ሆኖ ስላገኘው የውሳኔ ሀሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲላክ ወስኗል።

ጉባዔው ጉዳዩን መርምሮ የውሳኔ ሀሳቡን ሊያሳልፍ የቻለው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አስተዳደር ፍርድ ቤት ለጉባዔው የላከውን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ መነሻ በማድረግ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በስሩ ሠራተኛ በነበሩ አንድ ግለሰብ ላይ በዲሲፒሊን የጥፋተኝነትና የስራ ስንብት ቅጣት በመወሰኑ ነው።

በግለሰቡ ይግባኝ የቀረበለት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አስተዳደር ፍርድ ቤት በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና በሠራተኛው መካከል የነበረውን ክርክር ከተመለከተ በኋላ  ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ ለጉባዔው ልኳል። ጉባዔው ፍርድ ቤቱ የላከውን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ከአትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የሠራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች  ምክር ቤት  ደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀጽ 37 ‘’በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መስሪያ ቤት የሚሰራ ሰራተኛ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በሙስና የጠረጠረውንና እምነት ያጣበት ማንኛውም ሰራተኛ መደበኛውን የዲሲፕሊን እርምጃ አፈጻጸም ሳይከተል በተላለፈበት ውሳኔ ቅር በመሰኘት በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ስራ የመመለስ መብት የለውም’’ የሚለውን ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37/1/ ጋር የሚቃረን መሆን አለመሆኑን መርምሯል።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37/1/  ማናኛውም ሰው በፍርድ ቤት ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል። የሕገ መንግስቱን መርህ ተከትለው የወጡት ሕጎች ለማንኛውም የመንግሥት ሠራተኞች ተፈጻሚነት ያላቸው ሲሆን፣ ከዚህ በተለየ የሕገ መንግሥቱን መርህ ባልተከተለ መልኩ ለአትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሠራተኞች ብቻ ተብሎ የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀጽ 37 ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 37/1/ ጋር የሚጋጭ ስለሆነ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግስት ትርጉም  ያስፈልገዋል የሚል የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።

አራት አቤቱታዎች ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ ቀሪ ሁለት አቤቱታዎች ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ በይደር አልፏቸዋል።