ጉባዔው በስድስት የአቤቱታ መዛግብት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
November 17, 2023
በሰብአዊ መብት ላይ ለመወያዬት ወደ አልጀርስ ያቀናው ልኡክ የተሳካ ቆይታን አድርጎ ተመለሰ።
December 1, 2023
Show all

የአዋጅ ቁጥር 47/67 ክርክሮችና ሕገ መንግሥታዊነታቸው

በያደታ ግዛው

በ አዋጅ ቁጥር 47/67 መሰረት በመንግሥት በህጋዊ መንገድ ሳይወረሱ ከህግ ውጪ በመንግሥት የተያዙ የበርካታ ግለሰቦች ቤቶች የነበሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከአዋጁ ውጪ በተለያየ መንገድ በመንግሥት አላግባብ የተያዙ የግለሰብ ቤቶች በተለያዩ ጊዜያት ህግ በማውጣት ጭምር ቤቶቹ ለባለቤቶቹ እንዲመለሱ ሲደረግ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለዚህ ዓላማ ከወጡት አዋጆች ውስጥ አንዱ አዋጅ ቁጥር 110/88 አንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ አዋጅ መሰረት ከአዋጅ ቁጥር 47/67 ውጪ አለአግባብ በመንግሥት የተያዙ የግለሰብ ቤቶችን እያጣራ አንዲመልስ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ስልጣን ተሰጥቶት ነበር፡፡ ኤጀንሲውም በርካታ ጉዳዮችን በማጣራት በርካታ ቤቶችንም ለግለሰቦች ሲመልስ እንደነበር መዛግብት ያሳያሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዛሬም ጭምር ከአዋጅ ቁጥር 47/67 ውጪ በመንግሥት አላግባብ የተያዙ ቤቶች አንዲመለሱላቸው ለፍርድ ቤቶች እና ለተለያዩ አካላት አቤቱታዎች በመቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

አሁን በቀረበው ጉዳይ በፍርድ ቤት ከሳሽ የነበሩት ግለሰብ ከአዋጅ 47/67 መታወጅ ጋር በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሸን ላይ ክስ መስርተዋል፡፡ የክሱ ይዘትም በአዲስ አበባ በቀድሞ አጠራር ወረዳ 17 ቀበሌ 20 ክልል ውስጥ በካርታ ተመዝግቦ የሚገኝ መኖሪያ ቤት በደርግ ዘመን በቤቱ ውስጥ ከነበረው ንብረት ጋር ለቤት ሰራተኛ እና ለጥበቃ በአደራ ሰጥቼ ወደ ውጭ ሃገር ሄጄ ባለሁበት ቤቱን መንግሥት ከአዋጅ 47/67 ድንጋጌ ውጪ ስለያዘብኝ ይልቀቅልኝ በማለት ክስ አቅርበዋል፡፡ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታ ያቀረበው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሰጠው መልስ ቤቱ በመንግሥት የተወረሰ ስለመሆኑ፤ ከአዋጅ 47/67 ጋር የተያያዘ ክርክር ፍርድ ቤቶች ለማየት ስልጣን የሌላቸው ስለመሆኑ፤ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌዴሬሸን ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ከሰጠው ውሳኔ አንፃር የፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው እና የሕገ መንግሥቱን ፍትህ የማግኘት መብት የሚጥስ ስለመሆኑ ተከራክሯል፡፡

ክርክሩን የመረመሩት እና በየደረጃው ያሉት ፍርድ ቤቶች አከራካሪው ቤት ከአዋጅ 47/67 ውጪ አላግባብ በመንግሥት የተያዘ ስለመሆኑ፤ ተጠሪ ቤቱ አንዲመለስላቸው በከተማና ቤት ሚኒስቴር በተለያየ ጊዜ የተወሰነላቸው መሆኑን እንደምክንያት በመጥቀስ ቤቱ ለተጠሪ ሊመለስ ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ ውሳኔውም እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ፀንቷል፡፡

አመልካች የሆነው የፌዴራል ቤቶች ኮርፕሬሸን ለአጣሪ ጉባዔው ባቀረበው አቤቱታ በአዋጅ 47/67 የተወረሱ ቤቶችን በሚመለከት በተለይም ከአዋጁ ውጪ በሕገ ወጥ መንገድ በመንግሥት የተወሰዱ ቤቶችን አጣርቶ ለመመለስ በአዋጅ ቁጥር 110/88 መሰረት ስልጣን የተሰጠው ለፕራይቬታይዜሽን ኤጄንሲ ነው፡፡ ይህ ስልጣን በግልፅ ከፍርድ ቤቶች ተወስዶ ለሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን ላለው ለመንግሥት አካል የተሰጠ ሆኖ ሳለ ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ተቀብለው ማየታቸው እና ውሳኔ ወይም ፍርድ መስጠታቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 37(1) የተረጋገጠውን ፍትህ የማግኘት መብት የሚጥስ ስለመሆኑና በሌሎች በርካታ ነጥቦች ላይ አቤቱታ አቅርቧል፡፡

ጉባዔው የቀረበውን ጉዳይ መርምሮ ከአዋጅ 47/67 ጋር ተያይዞ የሚነሱ ክርክሮች ከሕገ መንግሥቱ ፍትህ የማግኘት መብት፤ ከንብረት መብት እና በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሰጠውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ቤቱ ለተጠሪ ሊመለስ አይገባም ሲል ወስኗል፡፡ ጉባዔው ለውሳኔው ሃሳቡ መሰረት ያደረጋቸው ነጥቦች አንደኛ ከአዋጅ 47/67 ጋር ተያይዞ በአዋጅ 110/1988 ተለይቶ ለፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ተሰጥቶ የነበረው የዳኝነት ስልጣን ከአዋጅ 47/67 ውጪ በሕገ ወጥ መንገድ በቀላጤ፤ በመመሪያ እና በቃል ትዕዛዝ የተወሰዱ ቤቶችን እያጣራ መመለስ ነው፡፡ ከአዋጁ ውጪ በመንግሥት አላግባብ የተወሰዱ ቤቶች በአዋጁ ላይ ከተደነገጉት ከእነዚህ ሁኔታዎች ውጪ በሌላ ሁኔታ ሊያዝ የሚችልበት አግባብ የለም፡፡ ከዚህ አንፃር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በሰጠው ውሳኔ በመንግሥት እጅ ለረዥም ጊዜ የቆዩ ቤቶችን በሚመለከት ከአዋጅ 47/67 ውጪ አላግባብ በመንግሥት መያዛቸው በፕራይዜታይዜሸን ኤጀንሲ ተጣርቶ ለግለሰቦቹ አንዲመለስ ካልተወሰነ በስተቀር ቤቱ አላግባብ በመንግሥት መያዝ አለመያዙን አሁን ከ40 ዓመት በኋላ ፍርድ ቤቶች በማስረጃ እያጣሩ ሊመልሱ አንደማይችሉ ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ ነው፡፡ 

በዚህ መዝገብ ላይ በቀረበው ጉዳይ ተጠሪ ጉዳዩን ከዚህ ቀደም ለፕራይዜታይዜሽን ኤጀንሲ አቅርበው ቤቱ ከአዋጅ 47/67 ውጪ በመንግሥት አላግባብ የተያዘ ስለመሆኑ አልተረጋገጠም ተብሎ በኤጀንሲው ውድቅ ተደርጎባቸዋል፡፡ ይህ በኤጀንሲው ተጣርቶ በመንግሥት አላግባብ የተያዘ ስለመሆኑ ያልተረጋገጠ ቤት ፍርድ ቤቶች በሌላ ማስረጃ አጣርተው ቤቱ በመንግሥት አላግባብ ከአዋጅ 47/67 ውጪ የተያዘ ነው በማለት ፍርድ መስጠታቸው በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን ፍትህ የማግኘት እና የንብረት መብት የሚጥስ ስለመሆኑ ጉባዔው የውሳኔ ሃሳብ ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አቅርቦ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሸን ምክር ቤት በሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳዮች ላይ የሚሰጠው ውሳኔ በመላ ሃገሪቱ በማናቸውም የመንግሥት አካል እና ተቋም ላይ ተፈፃሚነት ያለው እንደሆነ ከምክር ቤቱ አዋጅ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚሁ መሰረት ከአዋጅ 47/67 ውጪ አላግባብ በመንግሥት የተያዙ ቤቶችን በሚመለከት በአዋጅ 47/67 መጀመሪያ የከተማና ቤት ሚኒስቴር እያጣራ ሲመልስ የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ በአዋጅ 110/88 የፕራይዜታይዜሽን ኤጀንሲ ተቋቁሞ ከአዋጁ ውጪ አላግባብ በመንግሥት የተያዙትን ቤቶች ሲመልስ ነበር፡፡ በምክር ቤቱ ውሳኔ መሰረት ቤቶቹ ለረዥም ጊዜ በመንግሥት እጅ የቆዩ ከመሆናቸው እና ከጊዜው መቆየት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ የሰነዶች መጥፋት ጋር በተያያዘ ቤቶቹን ለግለሰቦቹ እንዲመለሱ ማድረግ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 37(1) የተረጋገጠውን መብት የሚጥስ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፤ ከዚህ አንፃር ዜጎችም ጉዳያቸውን ሲያቀርቡ የምክር ቤቱን ውሳኔዎች በአግባቡ በማጤንና መሰረት በማድረግ ሊሆን ይገባል የሚለው መልእክታችን ነው፡፡