ጉባዔው ከቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ላይ የመስማት /Public Hearing/ ስነ ሥርዓት አካሄደ
May 1, 2023
ሴንት ፒትርስበርግ በተካሄደው የአለምአቀፍ ስብሰባ ኢትዮጵያ ልምዷን አካፈለች
May 19, 2023

የመጀመሪያው የአፍሪካ እንስት ዳኞች ጉባዔ በጋቦን ሊብረቪሌ እ.ኤ.አ ከግንቦት 2 እስከ 6 ቀን 2023 ተካሄደ።

“በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የአፍሪካውያን እንስቶች ተሳትፎ” በሚል በአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤቶች እና መሰል ተቋማት ኮንፈረንስ አዘጋጅነት በሊብረቪለ በተካሄደው ጉባዔ ሕግ አውጭ አካሉ ሴቶች በፍትህ ተቋማት ላይ በአግባቡ እንዲወከሉ የሚያደርግበትን አሠራር ለመወያዬት እና መልካም ጅምሮችን ለማበረታታት መሆኑ ተመላክቷል።

 ከ35 ያላነሱ የአፍሪካ ሃገራት ተወካዮች በተሳተፉበት ጉባዔ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ የሴቶችን የመሪነት እና የተግባር ሚና ከወንዶች እኩል ለማድረግ ከማለም በተጨማሪ የአፍሪካ እንስት ዳኞች በሥራቸው የሚያጋጥሟቸውን መሰናክሎች በመለዬት መፍትሄ ለማበጀት ውይይቱ ተደርጓል።

በተጨማሪም እንስት ዳኞች የሚመለመሉበትን እና የሚሾሙበትን ሁኔታ እና ደረጃ ለመመዘን፣ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ የሴቶችን የመሪነት አቅም ለመረዳት፣ በፍትህ ተቋማት ላይ የሴቶች ተሳትፎ ያለውን በጎ ተፅዕኖ እውቅና ለመሥጠት፣ በፍትህ ተቋማት ላይ የሴቶችን የመሪነት ሚና ለመጨመር እና የፍትህ አሰጣጡን ለማሻሻል በጉባዔው  ላይ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶባቸው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በቅርብ ጊዜያት በተወሰኑ የአፍሪካ ሃገራት ተጨማሪ እንስት ዳኞችንና ዓቃቢ ሕጎችን የመሾም ሁኔታ ስለመኖሩ የተገለፀ ሲሆን የእንስት ዳኞች ቁጥር በተጨባጭ መጨመሩን እንዲሁም በጥቂት የአፍሪካ ሃገራት የእንስት ዳኞች ቁጥር ከጠቅላላው 50 በመቶ መድረሱ ተገልጿል። የተወሰኑ በጎ ጅምሮች ቢኖሩም በአፍሪካ የፍትህ ተቋማት ያለው የሥርዓተ ፆታ ውክልና እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ተመላክቷል። ለዚህም የባህል፣ የሕግ፣ የተቋም እና ማሕበራዊ ተግዳሮቶች በፍትህ ተቋማት ላይ የሴቶች ውክልና ዝቅተኛ ለመሆኑ ዋነኛ ምክንያቶች ተደርገው ተለይተዋል።

በዚሕ ጉባዔ ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያን በመወከል በፍትህ ተቋማት ላይ የሥርዓተ ፆታ ልዩነቱን ለማጥበብ በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት እየተደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ም/ፕሬዝዳንት እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ም/ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ናቸው።

ወ/ሮ አበባ እንደገለፁት በተለይም ባለፉት 4 ዓመታት በፌደራል  ፍ/ቤቶች ደረጃ የሥርዓተ ፆታ የውክልና ክፍተቱን ለመሙላት ተጨባጭ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል። ባለፉት ዓመታት የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት እንስት እንደነበሩ በማውሳት እና በአሁኑ ወቅትም የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ም/ፕሬዝዳንት ሴት መሆናቸውን በማስታወስ በአሁኑ ወቅት በፌዴራል ፍ/ቤቶች ካሉ 8 ዋና እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች 4ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በፍትሕ ሥርዓቱ  ላይ ያለው የሥርዓተ ፆታ አለመመጣጠን ችግር ከተቋሙም በላይ ነው ያሉት ወ/ሮ አበባ የሥራው ብዛትና የዳኞች ቁጥር ማነስ ሴቶች በቤተሰባዊ እና በማሕበራዊ ኃላፊነት ካለባቸው ተጨማሪ ኃላፊነት ጋር ተደራቢ ችግር መሆኑን አንስተው ይኸንን የሚቀርፍ ተጨማሪ ፖሊሲ ያስፈልጋል ብለዋል።

የፍትህ ሥርዓቱ ውክልና ብቻ ሳይሆን የማንኛውም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የማሕበረሰቡ ውክልና መሆን አለበት ያሉት ወ/ሮ አበባ ሴቶች የማህበረሰቡ ግማሽ በመሆናቸው 50 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ መያዝ እንዳለባቸው እና ሴቶች ራሳቸውን በራሳቸው ወክለው ማስተዳደር እንዳለባቸው አቋማቸውን አስረድተዋል።

በመጨረሻም ሴቶች ይበልጥ ለጥቃት ተጋላጭ እንደመሆናቸው መጠን በራሳቸው እኩል ተወካዮች ጥቃቱን በቀላሉ በሚረዱ እንስት ዳኞች ጉዳያቸው ቢታይ የተሻለ ፍትህ እንደሚሰፍን እምነታቸው መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ አበባ የሴቶችን የፍትህ እና መሰል ተቋማት ተመጣጣኝ ውክልና ለማምጣት ከማንም በላይ ሴቶች ራሳቸው በመተጋገዝ እና ራሳቸውን በማብቃት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።