ለጋብቻ የሚደረግ ጥበቃ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት
January 4, 2023
ጉባዔው በ70 ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
January 5, 2023
Show all

የመደራጀት መብት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት

በጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት

የመደራጀት መብት ማለት ሰዎች አንድን አላማ በጋራ ለማራመድ ወይም የጋራ ጥቅማቸውና ፍላጎታቸውን ለማሳካት ማሕበር የመመስረት መብት ነው፡፡ የመደራጀት መብት የአንድን ማሕበር አባል የመሆን መብት ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ከማሕበር አባልነት በፈቃደኝነት የመልቀቅ መብትንም ያጠቃልላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመደራጀት መብት በግልጽ በተቀመጠው የአባልነት መመዘኛ መስፈርት መሠረት መስፈርቱን የማያሟሉ ሰዎች በአባልነት ያለመቀበል መብት አካል ነው፡፡

በኢትዮጵያ በእቁብ እና በእድር እንዲሁም በሌሎች ማሕበራዊ እሴቶች የመደራጀት ታሪክ ረጅም ግዜ ያስቆጠረ ነው፡፡ የመደራጀት መብት የሰራተኞች ማሕበር አባል በመሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም፣ የሃይማኖት ድርጅቶች አባል በመሆን፣ የወንድማማችነት እና የስፖርት ድርጅቶችን በማቋቋምና አባል በመሆን እንዲሁም የሌሎች ማሕበራት አባል በመሆን ወይም ባለመሆን ሊገለጽ ይችላል፡፡ 

የመደራጀት መብት በ1987 ዓ.ም በጸደቀው ሕገ መንግሥት እውቅና እና ጥበቃ ከሚደረግላቸው መብቶች አንዱ ሆኖ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመደራጀት መብት ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች ለምሳሌ በአለም አቀፉ የሰቪልና የፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን እና በአለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት በወጡ ኮንቬንሽኖች እውቅና የተሰጠው ነው፡፡ የመደራጀት መብት በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ካላቸው መብቶች አንዱ ነው፡፡ የመደራጀት መብት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ እውቅና የተሰጠው በ1948ቱ ሕገ መንግሥት ነው፡፡

በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 23(4) መሠረት ማንኛውም ሰው ጥቅሙንና ፍላጎቱን ለማስከበር ማሕበር የመመስረትና በማሕበር የመደራጀት መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ አግባብ በአለም አቀፉ የሰቪልና የፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን አንቀጽ 22 መሠረት ማንኛውም ሰው የመደራጀትና ማሕበር የመመስረት መብት እንዳለው እውቅና ከሰጠ በኋላ የስምምነቱ ፈራሚ አገሮች ብሔራዊ ደህንነታቸውን፣ የማሕበረሰቡ ሰላምና ጸጥታ፣ ማሕበራዊ ጤና እና ሞራል ለመጠበቅ እንዲሁም የሌሎችን መብቶችና ነጻነቶች ለመጠበቅ የመደራጀት መብት በሕግ ሊገደብ እንደሚችል ደንግጓል፡፡ ከዚህ የምንረዳው የመደራጀት መብት ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች እውቅናና ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑን ነው፡፡ 

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 31 መሠረት “ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው” በማለት ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ለመረዳት የሚቻለው ማኅበሩ የሚመሰረትበት ዓላማ ግምት ውስጥ ሳይገባ ሰዎች ማሕበር የመመስረትና የመደራጀት መብት እንዳላቸው ነው፡፡ ከሕገ መንግሥቱ አላማ አንፃር አግባብነት ያለውን ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ መንግሥታዊ  ሥርዓቱን በሕገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ በማሕበር መደራጀት የተከለከለ ነው፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሃይል ወይም በሌላ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ለማፍረስ የሚመሰረቱ ማሕበራት ጥበቃ የማይደረግላቸው ሲሆኑ ማንኛውም ከሕግ የማይቃረን አላማ ለማሳካት የሚመሰረቱ ማሕበራት እውቅናና ጥበቃ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሰው የመደራጀት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ሰራተኞች ከአሰሪዎቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት በሕብረት ስምምነት ለመወሰን በማሕበር የመደራጀት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 42(1ሀ) እውቅና ተሰጥቶታል፡፡ የሰራተኞች የመደራጀት መብት አስፈላጊ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች መካከል ሰራተኞች በተናጥል ከአሰሪዎቻቸው ጋር ለመደራደር አቅም ስለማይኖራቸው በአሰሪዎቻቸው የጉልበት ብዝበዛ እንዳይደርስባቸውና ጥቅማቸውን ለማስከበር በሕብረት እንዲንቀሳቀሱ እድል ለመፍጠር ነው፡፡  

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 42(1ሀ) “የፋብሪካና የአገልግሎት ሠራተኞች፣ ገበሬዎች፣ የእርሻ ሠራተኞች፣ ከተወሰነ የኃላፊነት ደረጃ በታች ያሉና የሥራ ጠባያቸው የሚፈቅድላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የሥራና የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ለማሻሻል በማኅበር የመደራጀት መብት አላቸው” በማለት ደንግጓል፡፡ በግል ድርጅቶችና ፋብሪካዎች የሚሰሩ ሰራተኞች ከአሰሪዎቻቸው ጋር ለመደራደር በማሕበር የመደራጀት መብት ረዥም ግዜ ያስቆጠረ ሲሆን የመንግሥት ሰራተኞች ከስራቸው ባህሪ ጋር ተያይዞ ያላቸው የመደራጀትና የመደራደር መብት ወሰን አከራካሪ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በፋብሪካ፣ በአገልግሎት ዘርፍ ወይም በእርሻ የሚሠሩ ሰራተኞች የስራ ሁኔታቸውንና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር ከአሰሪዎቻቸው ጋር ለመደራደር የመደራጀት መብት አላቸው፡፡

የመደራጀት መብት ይዘት እና በመብቱ ላይ የተቀመጡት ገደቦችን አስመልክቶ በዝርዝር ሕግ እንዲሁም በሕገ መንግሥት ትርጉም እየዳበረ መሄድ ለሕገ መንግሥት እድገት ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የመደራጀት መብትን አስመልክቶ ሕግ አውጪው ዝርዝር ሕጎችን ያወጣ ሲሆን በተለይ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ፣ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት አዋጅ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ፣ የመኖሪያ ቤት ሕብረት ስራ ማሕበር መተዳደርያ እና ሌሎች አዋጆች የመደራጀት መብት ምንነትና ይዘት እንዲሁም ለመደራጀት መሟላት ያላባቸው መስፈርቶችን ያካተቱ ድንጋጌዎች ወጥተዋል፡፡

ከመደራጀት መብት አከባበር ጋር ተያይዞ በተለይ የማሕበር አባል የመሆን መብትን በተመለከተ፣ ከማሕበር አባልነት አለአግባብ ማፈናቀልን እና በማሕበር ውስጥ አንድ አባል ሊያገኝ ከሚገባው መብትና ግዴታ ጋር በተያያዙ የሚነሱ ክርክሮች በፍ/ቤት ወይም ስልጣን ባለው የዳኝነት አካል በመቅረብ ፍትሕ ለማግኘት ክርክሮች ይደረጋሉ፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 84(1) በተሰጠው ስልጣን መሠረት የመደራጀት መብትን አስመልክቶ በፍ/ቤት፣ በሕግ አውጪው ወይም በአስተዳደር አካላት ወይም ባለስልጣን የሚሰጡ ውሳኔዎች ሕገ መንግሥታዊነት በመመርመር ለሕገ መንግሥቱ እድገት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው፡፡ የመደራጀት መብትን አስመልክቶ የሚቀርቡ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎችና አቤቱታዎች እምብዛም ባይሆኑም የመደራጀት መብት ካለው አጠቃላይ ጠቀሜታ አንጻር በሂደት መሰል ጉዳዮች እንደሚበራከቱ መገመት ይቻላል፡፡

ዜጎች በሕገ መንግሥቱ በተረጋገጡላቸው መብቶች እንዲገለገሉ እና ግዴታቸውም እንዲፈጽሙ ከማድረግ ባሻገር የመደራጀት መብት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡት ሌሎች መብቶች ለማስከበር ጭምር በመሳሪያነት የሚያገለግል በመሆኑ በዚህ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ለሕገ መንግሥቱ አፈጻጸም ጠቃሚ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና አላማም ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውና ግዴታቸው እንዲያውቁ ለማስቻልና አጠቃላይ ማሕበራዊ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ላይ አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው፡፡ አንባብያን የመደራጀት መብትን አስመልክቶ ከፅሁፉ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ እምነት በመወሰድ በቀጣይም በሌሎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ላይ ፅሁፎች ይቀርባሉ፡፡ ለአሁን ቸር እንሰንብት፡፡