የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፌዴሬሽን ም/ቤትና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላት በሕገ መንግሥት ትርጉም ዙርያ የጋራ የምክክር አደረጉ
June 20, 2022
ጉባዔው በ 86 ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ
July 11, 2022

የመንግሥት ሠራተኛን በኃላፊ በተፃፈ ደብዳቤ ብቻ ከሥራ ማሰናበትሕገ መንግሥታዊ ነውን?

                                                     በያደታ ግዛው

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 37(1) መሰረት ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ያለው ስለመሆኑ ተደንግጓል። በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 42 ስር ለሠራተኞች የተደነገጉ በርካታ መብቶች አሉ። በተለይም ከዚህ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ አርዕስት መረዳት አንደሚቻለው ሠራተኞች በሕገ መንግሥቱ የተጠበቀላቸው የሥራ ዋስትና መብት ያላቸው መሆኑን መረዳት ይቻላል። በሕገ መንግሥቱ ለሠራተኞች የተጠበቀው የሥራ ዋስትና መብት ከሚከበርበት መንገድ ውስጥ አንዱ ሠራተኞች በሕግ አግባብ ከተቀመጠው ሂደት እና አሠራር ውጪ ከሥራቸው መባረር የሌለባቸው መሆኑ ነው። ሠራተኞች በሥራ ቦታ ለሚያጠፉት ጥፋት በሕግ አግባብ በተቀመጠው የዲስፕሊን ሂደት የመዳኘት መብት አላቸው። ይህ መብት ከላይ በተጠቀሰው የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 37(1) መሰረት የሚተገበር ነው።

በዚህ ድንጋጌ መሰረት በተለይም የመንግሥት ሠራተኞች በዲስፕሊን ጥፋት ከሥራ የሚሰናበቱት ጉዳያቸውን ለማየት እና ፍርድ ወይም ውሳኔ ለመስጠት በሕግ ስልጣን ባለው አካል ብቻ ነው። በሕግ በግልፅ ከተደነገገው አግባብ ውጪ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ተገቢውን ክርክር ሳያደርግ፤ ያለውን ማስረጃ በማቅረብ እራሱን ሳይከላከል አንዲሁም ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ላለው አካል ይግባኝ አቅርቦ ሳይከራካር ከሥራ ሊሰናበት አይችልም። አንድ ሠራተኛ ጥፋት ሲያጠፋ ተገቢው ክስ ቀርቦበት በቀረበበት ክስ ላይ ሠራተኛው መልስ ሰጥቶ የመከራከር፣ ማስረጃ የማቅረብ እና የመከላከል መብቱ ሊከበርለት ይገባል።

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 9(1) መሰረት ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ አንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ሆኖ ሲገኝ ተፈፃሚነት አንዳይኖረው በሕገ መንግሥት ትርጉም ስርዓት ውድቅ ይደረጋል።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 84 እና 9(1) ጣምራ ንባብ መሰረት ማንቸውንም ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ስልጣን አለው። በሚያደርገው ማጣራትም ማናቸውንም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ የባለስልጣን ወይም የመንግሥት አካል ውሳኔ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚጥስ ሆኖ ከተገኘ ተፈፃሚነት እንዳይኖረው የውሳኔ ሃሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል። ምክር ቤቱም የጉባዔውን የውሳኔ ሃሳብ ተቀብሎ ካፀደቀው ውሳኔው የመጨረሻ ይሆናል።

በዚሁ መሰረት ቀጥለን የምናየው ጉዳይ አስፈፃሚ የመንግሥት አካል የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ የክ/ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት የአንድን መምህር የዲስፕሊን ጉዳይ አስመልክቶ የሰጠው ውሳኔ ኢ-ሕገ መንግሥታዊነትን ነው።

አመልካች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ትምህርት ቤት መምህር ናቸው። እኝህ በአዲስ አበባ ከተማ በመምህርነት የሚያገለግሉ አመልካች በትምህርት ቤቱ ያሉ መምህራንን በማስተባበር የሥራ ማቆም አድማ አንዲደረግ አድርገዋል እንዲሁም የመማር ማስተማሩን ሥራ አስተጓጉለዋል በሚል በክ/ከተማው ትምህርት ፅ/ቤት ኃላፊ ደብዳቤ ከሥራ እንዲሰናበቱ ተደርጓል። አመልካች ይህን የክ/ከተማውን ፅ/ቤት ውሳኔ ለማሻር የይግባኝ ቅሬታ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት ሬጅስትራር ቢያቀርቡም ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን አልተቀበላቸውም። ቀጥሎም አመልካች አቤቱታቸውን ለሌሎች የተለያዩ የመንግሥት አካላት ቢያቀርቡም የሚቀበላቸው እና መፍትሄ የሚሰጣቸው አካል አላገኙም።

በመጨረሻም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን ለማጣራት ስልጣን ለተሰጠው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በአስተዳደር አካሉ ውሳኔ ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም አንዲሰጣቸው አመልክተዋል።

ጉባዔውም ጉዳዩን ለማጣራት ያመች ዘንድ አመልካች በወቅቱ ለአዲስ አበባ ሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት ሬጅስትራር የይግባኝ ማመልካቻ ማቅረብ አለማቅረባቸውን እና አንድ ጉዳይ በዲስፕሊን ኮሚቴ ሳይታይ በሥራ ኃላፊ ደብዳቤ ብቻ የተሰናበተ ከሆነ ለሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ እና መዝገብ ማስከፍት ይችላል ወይ የሚለውን አጣርቷል። ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ በወቅቱ የነበረው ሬጅስትራር የለቀቀ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ምላሽ መስጠት የማይቻል መሆኑን ጠቅሷል። በሌላ በኩል አንድ ጉዳይ በዲስፕሊን ኮሚቴ ሳይታይ በሥራ ኃላፊ በተፃፈ ደብዳቤ ከሥራ ቢሰናበት በዚሁ ደብዳቤ መነሻነት የይግባኝ መዝገብ መክፈት የሚቻል መሆኑን በመግለፅ መልስ ሰጥቷል።

አመልካች የስንብት ደብዳቤ በተሰጣቸው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የይግባኝ ማመልከቻ ለአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት አቅርበው የነበረ መሆኑን ለጉባዔው ካቀረቡት ማስረጃ መረዳት ይቻላል። በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት የአመልካችን ጉዳይ ተቀብሎ ማስተናገድ ሲገባው “አንቀበልም’’ ማለቱ አመልካች በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 37(1) የተረጋገጠላቸውን ፍትህ የማግኘት መብታቸው መጣሱን ያረጋግጣል።

የአመልካች ዓይነት የይግባኝ አቤቱታን የመቀበል፣ የመመርመር እና ፍርድ ወይም ውሳኔ የመስጠት ሕጋዊ ግዴታ የተጣለው በአዲስ አበባ ሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት ላይ ነው። ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በሕግ በተሰጠው የዳኝነት ስልጣን መሰረት የአመልካችን አቤቱታ በመቀበል ተገቢውን ማጣራት እና ክርክር በማድረግ ውሳኔ ወይም ፍርድ መስጠት ነበረበት። የአዲስ አበባ ሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት ይህን ኃላፊነቱን ባለመወጣት እና የአመልካችን አቤቱታ ተቀብለው ባለማስተናገዳቸው አመልካች ማግኘት የነበረባቸውን ፍትህ ሊያገኙ አልቻሉም።

ጉባዔው ጉዳዩን ካጣራ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት የአመልካችን ጉዳይ ተቀብሎ ማስተናገድ ሲገባው አንቀበልም ማለቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 37(1) ስር የተደነገገውን ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብቱን የሚጥስ ነው በማለት፣ አመልካች በፅ/ቤቱ ኃላፊ ደብዳቤ ብቻ የተላለፈባቸው የሥራ ስንብት ውሳኔ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው በማለት የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው የውሳኔ ሃሳቡን አሳልፏል።

ስለሆነም አመልካች ጉዳያቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት የማቅረብ መብት አላቸው በማለት ጉባዔው የውሳኔ ሃሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተላልፏል። ምክር ቤቱም የአጣሪ ጉባዔውን የውሳኔ ሃሳብ በመቀበል በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል።