ጉባዔው በ43 የሕገ መንግሥት አቤቱታዎች ላይ ብይን ሰጠ።
June 21, 2024
አጣሪ ጉባዔው በ54 አቤቱታዎች ላይ ውሳኔ እና አቅጣጫ አስቀመጠ።
July 12, 2024
Show all

የመብቶች ጥበቃና ሕገ መንግሥታዊ ክትትል ላይ አለምአቀፍ ውይይት እየተካሄደ ነው

በሩስያ ሴንትፒትስበርግ ከሰኔ 19-21 2016 ዓ.ም እየተካሄደ በሚገኘው የመብት ጥበቃና ሕገ መንግሥታዊ ክትትል /Protection of Rights and Constitutional Supervision/  አለምአቀፍ ውይይት ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንትና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ የሆኑት ክቡር አቶቴዎድሮስ ምህረት የሀገራቸውን ተሞክሮ አቀረቡ፡፡

በሩስያ ፌዴሬሽን ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤት ጋባዥነት በተዘጋጀው በዚህ ውይይት ክቡር አቶ ቴዎድሮስን ጨምሮ ከሀያ አምስት የአለም ሀገራት የተውጣጡ የሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤቶች ፕሬዚዳንቶች ተገኝተዋል፡፡

ክቡር አቶ ቴዎድሮስ የሀገራቸውን ተሞክሮ ሲያቀርቡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሰብአዊ መብትና ነፃነት ድንጋጌዎች ከአንቀፅ 13,- 44 ድረስ በስፋት እንደተቀመጡና አለም አቀፍ የሆኑ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችንም የሕጓ አካል እንዲሆኑ ማድረጓን ጠቁመዋል፡፡ እነዚህን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ለመተርጎም በኢትዮጵያ ያለው አደረጃጀት ለየት ያለ እንደሆነና ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ስልጣን የተሰጠው ለፌዴሬሽን ም/ቤት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ አክለውም የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔን አደረጃጀት፣ አሰራርና ተግባሩን በመጠቆም ጉባዔው በሕገ መንግሥት ትርጉም ረገድ ያለውን ሚና በስፋት አብራርተዋል፡፡ በዚህም ጉባዔው ጠንከር ያሉ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን በመመርመር የውሳኔ ሀሳቡን ለፌዴሬሽን ም/ቤት የሚልክ መሆኑን ቀደም ሲል በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ በወደቀበትና የመንግሥት የስልጣን ጊዜ ባለቀበት ወቅት ሕገ መንግሥቱን በመመርመር አጣጥሞ በመተርጎም መፍታት መቻሉን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ከሩስያው አቻቸው ከሚስተር ቫርሊ ዞርኪን ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያና በሩስያ መካከል ያለው ትብብር ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ የሁለትዮሽ ምክክር አድርገዋል፡፡ የሁለትዮሽ ምክክሩ ከኢንዶኔዥያ፣ ከህንድ፣ ከታይላንድና ከማሌዥያ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤቶች ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንቶችም ጋር በተመሳሳይ እንደተደረገ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡