የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አርባ አቤቱታዎችን መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ አቀረበ
September 19, 2018
ጉባዔው በሁለት ጉዳዮች ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥባቸው ለፌ/ም/ቤት የውሳኔ ሃሳብ አቀረበ
October 26, 2018

የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ጽ/ቤት ሰራተኞች የሰንደቅ አላማ ቀንን በደማቅ ሁኔታ አከበሩ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ጽ/ቤት ሰራተኞች ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ/ም በአገር አቀፍ ደረጃ “ሰንደቅ አላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን በሚል መሪ ቃል” ለ11ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሰንደቅ አላማ ቀን ብሄራዊ መዝሙር በመዘመር፣ ሰንደቅ ዓላማ በመስቀልና በሰንደቅ አላማ ዙሪያ ውይይት በማድረግ በደማቅ ሁኔታ አክብረዋል፡፡

የሰንደቅ አላማ አሰቃቀል ስነ ስርአት በጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዬሳ እና በሰራተኞች ተከናውኗል፡፡ የውይይቱ የመነሻ ፅሁፍ  በኮሙኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወ/ሮ ይርጋለም ጥላሁን የቀረበ ሲሆን በመነሻ ሃሳቡ የአገሪቷን ሰንደቅ አላማ ከአመጣጡ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በምን ደረጃ ላይ እንደሆነ ያብራሩ ሲሆን በተለይ ይህችን አገር ያቆዩዋት ጀግኖች አባቶች ለዚች ሰንደቅ አላማ መስዋዕትነት በመክፈል የሀገራቸውን ስም ከፍ እንዳደረጉ አብራርተዋል፡፡

አርማን በተመለከተ የዓለም አገራት ሰንደቅ አላማን ከአርማ ጋር በአንድ ላይ እንዲሁም ሰንደቅ አላማና አርማን ለያይተው የሚጠቀሙ እንዳሉ ጠቁመው በሀገራችን ዜጎች የጋራ የሆነውን ሰንደቅ አላማና ሀገራዊ አርማ ከድርጅት ሰንደቅ አላማና አርማ በመለየት በየቦታቸው መጠቀም እንደሚጠበቅባቸውም ገልፀዋል፡፡

የመነሻ ፅሁፍ ከቀረበ በኋላ ሰራተኞች በአንድ በኩል የአገራችን ባንዲራ የአንድነትን መግለጫ ከመሆኑም ሌላ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት የነፃነት መሰረት በመሆኑ እንደ ከፍተኛ ጥቅም መታየት እንዳለበትና አርማው ግን ልክ እንደባንዲራው በሕገ መንግስቱ ውስጥ በዝርዝር መገለፅ እንደነበረበት፣ የሀገርና የክልል ሰንደቅ አላማዎችና አርማዎችን መቼ፣ የትና እንዴት መጠቀም እንደሚገባ ሰፊ ትምህርት መሰጠት እንደሚገባ፣ በሌላ በኩል አርማው የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ያላስከበረ በመሆኑ ህዝቦችን ስለማይወክል መኖር የለበትም የሚሉ አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡

በቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ አቶ ደሳለኝ ወዬሳ ሰንደቅ አላማው በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 3 በግልፅ የተደነገገ መሆኑን፣ አርማው ሁሉንም አይወክልም ለሚለው የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነትን ለማመልከት በሕገ መንግስቱ የፀደቀ እንደሆነ፣ ብሄር ብሄረሰቦች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያሳድጉና ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ሕገ መንግስቱ ዕውቅና ቢሰጥም የአፈፃፀም ችግር ሊኖር እንደሚችል ጠቁመው በአጠቃላይ ግን ሕዝቡ ሰንደቅ ዓላማን የማክበር ሃላፊነት እንዳለበት እንዲሁም ሁሉም የመንግስት አካል በዚህ ዙሪያ የግንዛቤ ማስበጫ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ይርጋለም ጥላሁን በበኩላቸው በሰንደቅ ዓላማና አርማ ጉዳይ ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አለመሰራቱን መንግስትም እንደተረዳ፣ በተለይ በሰንደቅ ዓላማና አርማ  ልዩነት ላይ ዜጎች ጠለቅ ያለ ግንዛቤ የሌላቸው በመሆኑ የተፈጠረውን መወዛገብ ለማጥራት ይህ የመነሻ ፅሁፍ ሊቀርብ እንደቻለ፣ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው ዓርማ ሁሉንም አይወክልም የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ይወክለናል የሚሉ መኖራቸውን ታሳቢ ማድረጉ ለመደማመጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር፣ ሰንደቅ አላማ ሲታሰብ አገራዊ አንድነትን ማየቱ ጠቃሚ እንደሆነ ተናግረው ሁሉንም የሚወክል የጋራ አርማ ለማስቀመጥ መደማመጥና ስምምነት እንደሚያስፈልግ አስታወቀዋል፡፡