“በሕገ መንግሥት አተረጓጎም ሂደት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በወቅቱ ለማስተካከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶችን ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡” የጉባዔው ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዬሳ
January 6, 2022
የጉባዔው የቀድሞ አባላት አዲስ ለተሾሙ የጉባዔ አባላት ልምዳቸውን አካፈሉ
January 21, 2022

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እስካሁን ላከናወናቸው ተግባራት ታላቅ ክብርና ምሥጋና እንዳላቸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩⵆ

ክብርት ፕሬዳንቷ ሰኞ ጥር 9 ቀን 2014 ዓ.ም አጣሪ ጉባዔው የአገልግሎት ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የጉባዔውን አባላት በመሸኘት አዲስ የተሾሙ አባላቱን ለመቀበል ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ለቀድሞ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባላት ምስጋናና ሽኝት እንዲሁም ለአዳዲስ የጉባዔው አባላት አቀባበል በማድረግ የሥራ መመሪያም ሰጥተዋል።

ፕሬዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ መብትን በማስከበር ውስጥ እያበረከተ ላለው አስተዋፅኦ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ ማንኛውም ውሳኔ የተሰጠበት አካል ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል ብሎ ካመነ በተቋሙ በኩል ጉዳዩን ማቅረብ ይችላል ብለዋልⵆ

ሕገ መንግሥት ማለት የመንግሥት ተቋማትን የሚገልፅ፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካል ትሥሥርን የሚፈጥር፣ የመንግሥትንም ሥልጣን የሚገድብ እንዲሁም የሀገራችንን ሕዝብ የሚመስል መንግሥት ለመመስረት የሚጠቅም ሰነድ መሆኑን የገለጹት ክብርት ፕሬዝዳንቷ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የሕዝቡ ጤንነት አደጋ ላይ በመውደቁ በ2012 ዓ.ም ሊደረግ የነበረውን ምርጫ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲሰጥ በማድረግ አጣሪ ጉባዔው የምርጫ ጊዜው እንዲራዘም ያደረገበት መንገድ የሕገ መንግሥት አተረጓጎምን በአንድ ደረጃ ከፍ አድርጎታል ብለዋልⵆ

በመጨረሻም ሀገራችን አሁን ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ የፍትህ ስርዓቱን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አዳዲስ የጉባዔው አባላት የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ተቋቁመው ኃላፊነታቸውን በትጋት እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አረዳ በበኩላቸው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እና የፌደሬሽን ም/ቤት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሰረት የሕገ መንግሥት ትርጉም ይሠጣሉ ብለዋልⵆ

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 82 መሠረት አጣሪ ጉባዔው 11 አባላት እንደሚኖሩት የተናገሩት አቶ ሰለሞን፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት ሰብሳቢ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ምክትል ሰብሳቢ፣ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት የሚሾሙ በሙያ ብቃታቸውና በስነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ስድስት የሕግ ባለሙያዎች እንዲሁም የፌደሬሽን ም/ቤት ከአባላቱ መካከል የሚወክላቸው ሦስት ሰዎች የጉባዔው አባላት እንደሚሆኑ አስረድተዋልⵆ

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ 2005 ዓ.ም ጀምሮ ጽ/ቤት በማደራጀት ከ6ሺ በላይ አቤቱታዎች ቀርበውለት፣ ከ3ሺ በላይ የሚሆኑ ጉዳዮችን መመልከቱን ያስታወሱት አቶ ሰለሞን፣ አብዛኞቹ ጉዳዮች ከፍ/ቤት የመጡ እንደሆኑ በመግለፅ ከቀረቡት ጉዳዮች ውስጥ 102 የሚሆኑ ጉዳዮች የሕገ መንግሥት ትርጉም ተጠይቆባቸዋል ብለዋልⵆ

በአጣሪ ጉባዔው ተጣርተው በፌደሬሽን ም/ቤት ውሳኔ ካገኙ ጉዳዮች መካከል የ2012 ዓ.ም ሀገራዊ የሕዝብ ተወካዮች ምርጫና በኮቪድ19 ወረርሽኝ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶበታልⵆ

የምርጫ መራዘም አለመራዘም የቀጥታ የሚድያ ሽፋን ማግኘቱን የጠቀሱት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አረዳ፤ በጉዳዩ ላይ በርካታ ክርክሮች ከተደረጉበት በኋላ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት መወሰኑን አስታውሰዋልⵆ አቶ ሰለሞን በሀገሪቱ ታሪክ ግልፅና ቀጥተኛ ነበር ባሉት የምርጫ መራዘም ጉዳይ አዲስ መንግሥት እስኪመሰረት የነበረው እንዲቀጥል ተወስኖ እንደነበር አስታውሰዋልⵆ በሌላ በኩል የፌደራሉን ሕገ መንግሥት በሚፃረር መልኩ ምርጫ ቦርድ በማቋቋም የትግራይ ክልል ያደረገው ምርጫ፤ተፈፃሚነት የሌለውና እንዳልተደረገ የሚቆጠር መደረጉን የተናገሩት አቶ ሰለሞን፤ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን መቋቋምን በተመለከተ ከትግራይ ክልል ለአጣሪ ጉባዔው “ሕገ መንግሥቱን ይፃረራል” በሚል የቀረበው ጉዳይ አዋጁ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የማይጥስ እንደሆነ በመረጋገጡ አቤቱታው ውድቅ ተደርጓል ብለዋልⵆ ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ፍትህ የማግኘት፣የገቢዎች ሚኒስቴር ያወጣው ሠራተኛን የማባረር አዋጅ፣የመኖሪያ ቤት አዋጅ፣የሴቶችና ሕፃናት መብት፣የውርስ መብት፣ የአረጋውያን መብት፣ እና መሰል ጉዳዮች የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደተሰጠባቸው አቶ ሰሎሞን አሰረድተዋልⵆ

አዲስ የተሾሙ የጉባዔው አባላት ጉባዔው ሥራውን በአግባቡ እንዲሠራ በማድረግ፣ ስለጉባዔው ግንዛቤ በመፍጠርና ዜጎች በጉባዔው ላይ እምነት እንዲያሳድሩ በማድረግ አጣሪ ጉባዔውን ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የጉባዔው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋልⵆ

ሕገ መንግሥታዊነትን ማስፈን ሀገርን ማፅናት ነው ያሉት በአጣሪ ጉባዔው ለ4 ተከታታይ የጉባዔው የአገልግሎት ዘመናት በጉባዔ አባልነት ያገለገሉት ክቡር ዶ/ር ፋሲል ናሆም ናቸውⵆ ዶ/ር ፋሲል እንደሚሉት፤ መንግሥት የተሾመው የሕዝብን መብት ለማስከበር ነውⵆ

አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥት በቅርፅ ፌደራላዊ በይዘት ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መሆኑን የገለፁት የቀድሞ የጉባዔው አባል ዶ/ር ፋሲል፤ እስካሁን ወደ አጣሪ ጉባዔው የሚመጡ ጉዳዮች በፍርድ ቤቶች በኩል አልፈው ፍትህ ተጓደለብን የሚሉ መሆናቸውን አስታውሰዋልⵆ

በፕሮግራሙ አዳዲስ የተመረጡ የጉባዔው አባላት ቃለ መሀላ የፈፀሙ ሲሆን ለቀድሞዎቹ የጉባዔው አባላት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋልⵆ