የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሐሙስ ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ጉባዔ በአምስት የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በዕለቱ በተደረገው ጉባዔም ሁለት የአቤቱታ መዛግብት ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ጉዳዮቹን ከመወሰን ባሻገር በጉዳዮቹ ላይ የዳበረ ሀሳብ ቢቀርብበት ሕገ መንግሥታዊ የአተረጓጎም ስርአቱን ለማጠናከርና ለፍትህ አካላትም ተጨማሪ ግንዛቤ ለመፍጠር ይረዳል የሚል ግምት በማሳደሩ በዘርፉ ልምድ ካላቸው የሕግ ምሁራንና ከተቋማት ሙያዊ ሃሳብ እንዲቀርብበትና የመሰማት ሂደት (hearing) መድረክ እንዲካሄድባቸው ጉባዔው አቅጣጫ ሰጥቷል።
በሌላ በኩል በዕለቱ የታዩ ሌሎች ሁለት የሕገ መንግሥት የአቤቱታ መዛግብት ላይ ተጨማሪ ጥናት እና የማስረጃ ማጣራት ተደርጎባቸው ለቀጣይ ጉባዔ እንዲቀርቡ ጉባዔው አመላክቷል።
በመጨረሻም በአንድ መዝገብ ላይ በአመልካችና በተጠሪ በተደረገ ስምምነት መሰረት የትርጉም አቤቱታው እንዲቋረጥ በመጠየቁ ጉባዔው እንዲቋረጥ ወስኗል።