የጉባዔው ጽ/ቤት አመራርና ሠራተኞች የፀረ ሙስና ቀንን አከበሩ
December 5, 2020
ጉባዔው በአንድ ሕገ መንግስታዊ ጉዳይ ላይ የውሳኔ ሀሳብ አሳለፈ
February 1, 2021

የሕገ መንግሥት አተረጓጎምና የውሳኔ አፈፃፀም ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም አካል የራሱን ሀላፊነት መወጣት እንዳለበት ተጠቆመ

የሕገ መንግሥት አተረጓጎምና የውሳኔ አፈፃፀም ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም አካል የራሱን ሀላፊነት መወጣት እንዳለበት ተጠቆመ

በሕገ መንግሥት አተረጓጎምና የውሳኔ አፈፃፀም ችግሮች እንዲሁም መፍትሄዎቻቸው ላይ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ም/ቤት እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ ከዳኞችና ከህግ ባለሙያዎች ጋር ጥር 8 ቀን 2013 ዓ.ም ውይይት አደረጉ፡፡

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢና የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንደገለፁት የሕገ መንግሥት ትርጉም ስርአት በየጊዜው እየዳበረ የሚሄድ ከመሆኑ አንፃር ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እንደነዚህ ባሉ መድረኮች ከፌዴሬሽን ም/ቤት፣ ከፍ/ቤቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረግ የሕገመንግሥት ስርአቱን ለማጠናከርና የሕገመንግሥት የበላይነትን በማረጋገጥ ፍትህን ለማስፈን ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

 

የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው በመክፈቻ ንግግራቸው የፌዴሬሽን ም/ቤትና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሕገ መንግሥት የበላይነትን ለማረጋገጥ ዜጎች በሕገ መንግሥቱና በሕገመንግሥታዊ ስርአቱ ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያቀርቧቸውን የሕገመንግሥት ትርጉም ጥያቄዎች ጥራቱን በጠበቀና በተፋጠነ ስርአት ውሳኔ ማግኘት እንዲችሉ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ረገድ ቀጣይነት ያለው ስራ መሰራት እንደሚኖርበት ገልፀዋል፡፡

ለውይይቱ መነሻ የሆነ የጥናት ፅሁፍ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ፅ/ቤት የሕገ መንግሥት አስተምህሮ ቡድን መሪ በሆኑት አቶ ያደታ ግዛው የቀረበ ሲሆን ከሕገ መንግሥት አተረጓጎምና ውሳኔን ከማስፈፀም አንፃር የሚታዩ ችግሮችን በማንሳት መፍትሄዎችን ጠቁመዋል፡፡ በችግሮቹና መፍትሄዎቹም ላይ የፌዴሬሽን ም/ቤት፣ የአጣሪ ጉባዔው እንዲሁም የፍ/ቤቶች ሚና ምን እንደሚመስል አቅርበዋል፡፡

 

በቀረበው ፅሁፍ ላይ በተሳታፊዎች ሰፊና ጥልቅ የሆነ ውይይት የተደረገ ሲሆን ሕገመንግሥትን መተርጎም ትልቅ ስራ መሆኑን ህብረተሰቡን ማስገንዘብ አስፈላጊ እንደሆነ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔም ሆነ የውሳኔ ሀሳቦች ሲዘጋጁ በማንና እንዴት እንደሚፈፀም የስነ ስርአት ህጎችን ባገናዘበ መልኩ ግልፅ መሆን እንዳለበት፣ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላም አፈፃፀሙን የሚከታተል ጠንካራ መዋቅር መዘርጋት እንዳለበት፣ ከእግድና ከይርጋ ጋር ተያይዞ የሚመጡ አቤቱታዎች ከአቅም በላይ በመሆናቸው መፍትሄ መበጀት እንዳለበት፣ ም/ቤቱም ሆነ አጣሪ ጉባዔው በህግ በተሰጣቸው ስልጣን ላይ አተኩረው ቢሰሩ የሚሉና ሌሎችም በርካታ ሀሳቦች ተነስዋል፡፡

 

ክብርት ወ/ሮ መዓዛም በውይይቱ የቀረቡት ሀሳቦች ጥሩ ግብአት እንደሚሆኑ ጠቁመው የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔዎችን ማክበር እንዲኖር ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ፣ ከሌሎች አስፈፃሚ አካላትም ጋር የጋራ መድረክ እንደሚያስፈልግ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የውሳኔ አፈፃፀምን በተመለከተም የአሰራር መመሪያ መውጣት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በማጠቃለያ ምየተከበሩ አቶ አደም ፋራህ በውይይቱ ከተነሱት ሀሳቦች ም/ቤቱ፣ አጣሪ ጉባዔውና ፍ/ቤቶች መወጣት ያለባቸው ሀላፊነት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ በም/ቤቱ በኩል የሪፎርም ስራ እየተሰራ በመሆኑ የተነሱት ነጥቦች በግብአትነት እንደሚካተቱ ጠቅሰው የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የቅንጅት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስምረውበታል፡፡