የጉባዔው ጽ/ቤት አመራርና ሠራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ
August 9, 2022
ጉባዔው በ29 ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ 27ቱ ላይ ውሳኔ አሳለፈ
August 24, 2022

የህፃናት ሕገ መንግሥታዊ መብት ከአሳዳጊዎቻቸው የሃይማኖት ነፃነት አንፃር

በያደታ ግዛው

ውድ አንባብያን ባለፉት እትሞቻችን የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በተለያዩ ጊዜያት አጣርቶ የውሳኔ ሃሳብ አሳልፎባቸው በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙ እና ለህብረተሰቡ እና ለህግ ባለሙያዎች በአስተማሪነታቸው የታመነባቸው ጉዳዮች ስናቀርብላችሁ ቆይተናል፡፡ በዛሬው እትማችንም ከአሳዳጊዎቻቸው የእምነት ነፃነት አንፃር የህፃናት ሕገ መንግሥታዊ መብት ምን ይመስላል የሚለውን እናቀርብላችኋለን፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 36 የህፃናት ሕገ መንግስታዊ መብቶች ተደንግገዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 34 (4) መሰረት የግል እና የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ በተከራካሪዎች ፍቃድ በሃይማኖት እና በባህል ሕጎች መሰረት የመዳኘት መብት ተከብሯል፡፡ እነዚህ ሁለቱን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በሚመለከት  ለአጣሪ ጉባኤው የቀረበ እና የውሳኔ ሃሳብ የተላለፈበትን አንድ ጉዳይ እነሆ፡፡

ለአጣሪ ጉባኤው የቀረበው ጉዳይ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ሸሪዓ ፍ/ቤት ሲሆን አቤቱታ ያቀረቡት ተጠሪ (የህፃኗ አባት) ናቸው፡፡ የተጠሪ አቤቱታ በአመልካች (የህፃኗ እናት) ላይ ባቀረቡት ሞግዚትነትን ይሰረዝልኝ አቤቱታ መነሻነት ነው፡፡ የአቤቱታው ይዘት በአጭሩ አመልካችና ተጠሪ መካከል የነበረው ጋብቻ በፍቺ የፈረሰው ግራ ቀኙ በሸሪዓ ፍርድ ቤት ለመዳኘት ፍቃድ ሰጥተው በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የግራ ቀኙ ጋብቻ ሲፈርስ በመካከላቸው የተወለደችው ህፃን ልጅ እናቷ ጋር ወይም አመልካች ጋር እንድታድግ እና የህፃኗ አባት ደግሞ በየወሩ ብር 2,500 ቀለብ እንዲቆርጥ ተወስኖ ነበር፡፡ የሞግዚትነት ውሳኔ በፍ/ቤት በሚሰጥበት ወቅት አመልካች (የህፃኗ እናት) የእስልምና እምነት ተከታይ ነበሩ፡፡

ነገር ግን  አመልካች (የህፃኗ እናት) የህፃኗ አሳዳጊነት ውሳኔ በፍርድ ቤት ከተሰጠ በኋላ የእስልምና እምነታቸውን ቀይረዋል፡፡ በዚሁ ምክንያት ተጠሪ (የህፃኗ አባት) አሁን የሚያቀርቡት አቤቱታ ለአመልካች (ለህፃኗ እናት) በፍርድ ቤት ተሰጥቷት የነበረው የሞግዚትነት ውሳኔ እንዲሰረዝ የሚል ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የህፃኗ እናት የእስልምና እምነቷን ቀይራ ልጄንም የክርስትና እምነት ተከታይ እንድትሆን እያደረገች ነው በሚል ነው፡፡

ክርክሩን የተመለከተው ፍ/ቤቱም በሸሪዓው ሕግ የልጆች አሳዳጊ የሆነ ወገን ሊያሟላቸው ከሚገቡ መስፈርቶች ውስጥ አንዱ ልጅ አሳዳጊ የሆነው ወገን በእምነቱ የፀና መሆን አንዳለበት ነው፡፡ ነገር ግን የህፃኗ እናት በተደጋጋሚ እምነታቸውን እንደሚቀያይሩና በአንድ እምነት የማይፀኑ መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ ስለሆነም የህፃኗ እናት ከሸሪዓ ሕጉ አኳያ ህፃኗን ለማሳደግ መስፈርቱን የማያሟሉ ስለሆነ በፍርድ ቤት ተሰጥቶአቸው የነበረው የአሳዳጊነት ውሳኔ ተሰርዞ ህፃኗ ከአባቷ ጋር እንድታድግ እና እናት ልጇን በየ 8 ቀኑ አንድትጎበኝ ሲል ወስኗል፡፡ ውሳኔውም እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ፀንቷል፡፡

አመልካች ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ባቀረቡት አቤቱታ በሕገ መንግሥቱ ተፈቀደውን ሃይማቴን የመቀየር መብቴን በሚፃረር መልኩ በፍርድ ቤቶች የልጄ አሳዳጊ እንዳልሆን የተሰጠው ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊ መብቴን የሚጥስ ነው፡፡ ከፍቺ ውሳኔ በኋላም ሀይማኖቴን የቀየርኩ በመሆኑ በሸሪዓ ፍ/ቤት ለመዳኘት ፍላጎት እንደሌለኝ ለችሎቱ በመግለፅ መቃወሚያዬን አቅርቤ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል የፌዴሬሽን ም/ቤት በወ/ሮ ከድጃ በሽር እና በወ/ሮ ራንያ አህመድ በሰጠው የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔ ያለተከራካሪዎች ፍቃድ በሃይማኖት ፍርድ ቤት መዳኘት ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነው ብሏል፡፡

ጉባዔውም አመልካች ያቀረቡትን አቤቱታ ከሕገ መንግስቱ አንቀፅ 34/5/፣ 35/1/ እና /2/፣ 27 /1/ እና /3/፣ 36 /2/ አንፃር በመመርመር ሁለት መሰረታዊ የሕገ መንግሥት ነጥቦችን መሰረት አድርጎ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡

1ኛው አመልካች ከተጠሪ ጋር በፍች ከተለያዩ በኋላ ሃይማኖታቸውን በመቀየራቸው በሸሪዓ ፍርድ ቤት ለመዳኘት ፍቃደኛ አይደለሁም እያሉ የተሰጠው ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊነት ሲሆን 2ኛው የልጅ ሞግዚትነት ስልጣንን ለመወሰን በፍርድ ቤቶች በቀደምትነት ሊታይ የሚገባው ነጥብ ምን መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡

የመጀመሪያውን ነጥብ በተመለከተ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34(5) መሰረት የግልና የቤተሰብ ህግ በተከራካሪዎች ፈቃድ በሃይማኖታዊ ወይም በባህላዊ ሕጎች መሰረት መዳኘትን አይከለክልም፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት የሃይማኖት ወይም የባህል ተቋማት የዳኝነት ስልጣን በተከራካሪ ወገኖች ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የተከራካሪ ወገኖች ፈቃድ ከሌለ የዳኝነት ስልጣን አይኖረውም፡፡

ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ የፌዴራል የሸሪዓ ፍ/ቤቶችን ለማጠናከር በወጣው አዋጅ ቁጥር 188/92 አንቀጽ 4(2) በተመሳሳይ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 34(5) በተገለጸው መሰረት  ፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን የሚኖራቸው ተከራካሪ ወገኖች በእስልምና ኃይማኖት ሥርዓት ለመዳኘት ግልጽ በሆነ መንገድ ፍቃዳቸው ከሰጡ ነው፡፡

የኃይማኖት ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣንን ከመተግበራቸው በፊት ባለጉዳዮች በፍርድ ቤቱ እና በህጉ ለመዳኘት ፈቃደኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ከዚህ አንፃር የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወ/ሮ ከድጃ በሽር ጉዳይ ተመሳሳይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ መሰረት አመልካች (የህፃኗ እናት) ለቀረበባቸው ክስ መልስ ሲሰጡ ወደ ክርስትና እምነት የተመለሱ መሆኑን በመጥቀስ በሸሪዓ ፍ/ቤት ለመዳኘት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህንኑ መቃወሚያ መሰረት በማድረግ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት መወሰን ሲገባቸው ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ውጪ በአመልካች ጉዳይ ላይ በሃይማኖት ፍርድ ቤት ውሳኔ መስጠታቸው ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነው፡፡

ሁለተኛውን ነጥብ በሚመለከት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 36(2) እንደተደነገገው ሕጻናትን የሚመለከቱ እርምጃዎች በሚወሰዱበት ጊዜ በመንግስታዊ ወይም በግል የበጎ አድራጎት ተቋሞች፣ በፍርድ ቤቶች፣ በአስተዳደር ባለስልጣኖች ወይም በሕግ  አውጪ አካላት የሕፃናት ደህንነት በቀደምትነት መታሰብ አለበት በማለት ይደነግጋል፡፡ አመልካችና ተጠሪ መካከል ያለው ክርክር ከሕጻን ሞግዚትነት ጋር የተያያዘ ሲሆን የአሁን ተጠሪ አመልካች የልጅቷን ሞግዚትነት ከአመልካች ለመውሰድ የአመልካችን እምነት መቀየር እንደመከራከሪያ አድርገው አቅርበዋል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የሸሪዓ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሆነ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 36(2) መሰረት ከእድሜዋ አንጻር ለሕጻኗ ትምህርት፣ ጤና፣ እድገት ማን ዘንድ ብታድግ የተሻለ ነው የሚለው በማህበራዊ ሰራተኛ ባለሞያ ተደግፎና ተጣርቶ መወሰን ሲገባው አልተጣራም፡፡

ጉዳዩ በአግባቡ ባለመጣራቱም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 36 ንዑስ አንቀጽ 1 (ሐ) እና ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ሕጻናትን የሚመለከቱ እርምጃዎች በሚወስዱበት ጊዜ በመንግሥታዊ ወይም በግል የበጎ አድራጎት ተቋሞች፣ ፍርድ ቤቶች፣ የአስተዳደር ባለስልጣኖች ወይም በሕግ አውጪ አካላት የሕፃናት መብትን (the best interest of the child) በቀደምትነት ማሰብ አለባቸው የሚለውን መርህ የተከተለ አይደለም፡፡ በመሆኑም ፍ/ቤቶቹ የአመልካችን ሕጻኗን የማሳደግ ስልጣን በመሰረዝ ተጠሪ እንዲያሳድግ በማለት የሰጡት ውሳኔ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 36 ንዑስ አንቀጽ 1(ሐ) እና ንዑስ አንቀጽ 2ን የሚጥስ ነው፡፡