ጉባዔው 35 የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
September 30, 2022
“… We have a great responsibility to shape the future of our society by establishing the rule of law and administrative justice.” Her Excellency Mrs. Meaza Ashenafi
October 20, 2022

ክብርት ሰብሳቢዋ በዓለም አቀፉ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና የመሰል ተቋማት ኮንፈረንስ ላይ አፍሪካን በመወከል ፅሑፍ አቀረቡ

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በኢንዶኔዢያ ባሊ ከተማ በተደረገው 5ኛው የዓለም አቀፉ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና የመሰል ተቋማት ኮንፈረንስ የምክክር ጉባዔ ላይ ተሳተፉ።

ክብርት ወ/ሮ መዓዛ ከኦክቶበር 04 እስከ 07/2022 የተካሄደው ጉባዔ ላይ የተሳተፉት በዙም ቴክኖሎጂ አማካይነት ሲሆን፣ አፍሪካን እና የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና የመሰል ተቋማት ማኅበርን በመወከልም በመክፈቻው ዕለት ጥናታዊ ፅሑፍ አቅርበዋል። በጉባዔው ላይ ፅሑፍ እንዲያቀርቡ የተመረጡት ሁለት የአፍሪካ ሀገሮች ሲሆኑ፣ እነሱም ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ ናቸው።

በጉባዔው ላይ የእስያ እና አፍሪካ የጋራ መድረክ ውይይት ተደርጓል። የውይይቱም ጭብጥ “የእስያና አፍሪካ ትብብር መሰረታዊ የሕዝቦችን ሰብዓዊ መብት ለመጠበቅ” (Promoting Asian-African Cooperation for the Protection of Peoples Fundamental Rights) የሚል ነበር።

ክብርት ሰብሳቢዋ ያቀረቡት ፅሑፍም “Actuating the ‘Bandung Principles’ on Equality of All People, Races, & Nations in Asia and Africa” በሚል ርዕስ ሲሆን፣ በፅሑፋቸውም የእስያና አፍሪካ ግንኙነት የበርካታ አስርት ዓመታት ታሪክ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያም ከብዙ የእስያ ሀገራት ጋር የረጅም ዓመታት ቋሚ ግንኙነት ያላት ሀገር መሆኗን አውስተዋል።

የጉባዔው የመወያያ ጭብጥ የሕገ መንግሥታዊነት መስፈን ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ የሚኖረው ሚና ላይ መሆኑ ከዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ1955 በኢንዶኔዥያ ባንደንግ በተደረገ ጉባዔ የተገባውን ቃልኪዳን የሚያጠናክር መሆኑን በፅሑፋቸው አንስተዋል።

አስሩ የባንደንግ መርሆች (the Ten Principles of Bandung) በመባል የሚታወቀው ድንጋጌ አስር አንቀፆችን የያዘ ሲሆን፣ ድንጋጌው የፀደቀውም እ.ኤ.አ በ1955 እስያና አፍሪካ ባደረጉት የጋራ ኮንፈረንስ ላይ ነው። ዓላማውም በዓለም ላይ ሰላም እና ትብብርን መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው።

ከአንቀፆቹ መካከልም በአንቀፅ 2 የተጠቀሰው “የሁሉንም ሀገራት ሉአላዊነትና የግዛት አንድነትን ማክበር” እና በአንቀፅ 4 የተጠቀሰው “በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ” የሚሉት ይገኙበታል። ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድና በድርድር መፍታት፣ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን ማክበር፣ ለፍትህ እና ለዓለም አቀፍ ግዴታዎች መገዛት የሚሉ እና ሌሎችም አንቀፆች በድንጋጌው ላይ ተካተው ይገኛሉ።

የፍትህ መስፈን ለሰው ልጆች እኩልነትና ሰብዓዊ መብት መከበር የሚኖረውን ሚና አስመልከተው ክብርት ሰብሳቢዋ ባቀረቡት ፅሁፍ ሲያስረዱ በርካታ ምሳሌዎችን የጠቀሱ ሲሆን፣ ከመንግሥት የፍትህ ተቋማት በተጨማሪ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ ማኅበራት፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋማት እና የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው አትተዋል።

ክብርት ወ/ሮ መዓዛ የኢትዮጵያን ተሞክሮ በተመለከተ አጣሪ ጉባዔው በገለልተኛነት ሥራውን ለመሥራት በሚያስችለው መልኩ እንዴት በባለሙያዎች እንደተዋቀረ ለተሰብሳቢው ያስረዱ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከምርጫ 2012 ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ በነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫን በወቅቱ ማድረግ ስላልተቻለ በጉባዔው የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በተሞክሮነት አውስተዋል።

በፅሑፋቸው ማጠቃለያ ላይም ዓለማችን በርካታ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጠች ያለች ቢሆንም የሕግ የበላይነትን እና አስተዳደራዊ ፍትህን በማስፈን የማኅበረሰባችንን መፃኢ ዕድል የመቅረፅ ትልቅ ኃላፊነት አለብን ሲሉ ለኮንፈረንሱ ታዳሚዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።