አዲስ በተሾሙት ሰብሳቢዎች የተመራው አጣሪ ጉባዔሁለተኛ ጉባዔውን አከናወነ
February 16, 2023
አጣሪ ጉባዔው በሁለት የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ላይ ውይይት አካሄደ።
February 24, 2023
Show all

ከሕገ መንግሥት አተረጓጎም ጋር በተያያዘ የጉባዔውና የፍ/ቤቶች የስልጣን ወሰን ላይ ውይይት ተደረገ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ምሁር ዶ/ር ዘመላክ አየለ  የቀረበው እና በሕገ መንግሥት  አተረጓጎም ዙሪያ ከሌሎች ሃገራት ልምድና ተሞክሮ አንፃር የተጠናው ፅሁፍ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢዎች እና አባላት እንዲሁም የጉባዔ ጽ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ሐሙስ የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱም የሕገ መንግሥት ትርጉም ምንነት፣ የአተረጓጎም አይነቶችና ዘዴዎች፣ የተለያዩ ሃገራት ተሞክሮዎች እና በአጣሪ ጉባዔው እና በፌዴሬሽን ም/ቤት የተሰጡ የሕገመንግሥት ትርጉም ውሳኔዎች ለማሳያነት ቀርበዋል።

በውይይቱም የአጣሪ ጉባዔው ሥልጣንና ተግባር ከፍርድ ቤቶች ሥልጣንና ተግባር ጋር  የሚለይባቸውን ነገሮች ማለትም ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይን መተርጎም ሕግን ከመተርጎም በግልፅ እንዴት መለየት ይቻላል፣ በተለይ ከፍ/ቤት የመጨረሻ ውሳኔ አግኝተው የመጡ ጉዳዮች ላይ ሕገመንግሥታዊ ጉዳይ ሊነሳ የሚችለው ውሳኔው ላይ? ሕጉ የተተረጎመበት መንገድ ላይ? የተጠቀሰው ሕግ ላይ? ወይስ የፍርድ አሠጣጥ ሂደቱ ላይ  በሚለው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡የጥናቱ ዓላማም አጣሪ ጉባዔው የፍርድ ቤቶችን ሥልጣን በማይጋፋ መልኩ ሥራውን እንዲሠራ ለማስቻል መሆኑን የአጣሪ ጉባዔ ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ደሳለኝ ወዬሳ ጠቁመዋል።

ጥናቱ የጉባዔውን አዋጅ እና መመሪያ ላይ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች ታይተው የተሻለ አሠራር ለማስቀመጥ በሚያስችል መልኩ በይበልጥ ተዘጋጅቶ ቢቀርብ፣ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ የአሰራር መመሪያ ማውጣት ቢቻል የሚሉና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች በጉባዔው አባላት ተነስተዋል፡፡

በጥናቱ ከተጠቆመው በተጨማሪ ጉባዔው በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 84 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የፍርድ ቤቶች ሥልጣን የሚያልቅበት እና የአጣሪ ጉባዔው የሚጀምርበት በግልፅ በሚያሳይ መንገድ በፅ/ቤት ደረጃ አጭር ጥናት ቢደረግ ፣  በሌላ በኩል በተጠቃለለ መልኩ የትኛውን የትርጉም ሞዴል እንከተል ከሚለው ፅንሰ ሐሳብ ጀምሮ የግለሰቦች መብት መጣስ ከሕገ መንግሥት ትርጉም አንፃር የሚሥተናገድበት፣ ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ አንፃር አዋጁና ደንቡን በመፈተሽ ግልፅ የሆነ አሰራር መዘርጋት የሚያስችል ጥናት በውስጥ ወይም በውጭ ባለሙያዎች ተጠንቶ እንዲቀርብ የአጣሪ ጉባዔው ሰብሳቢ ክቡር አቶ ቴዎድሮሥ ምህረት አሳስበዋል።