አጣሪ ጉባዔው በ32 የሕገ መንግሥት የትርጉም አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እና አቅጣጫ አስቀመጠ።
May 17, 2024
ጉባዔው በ7 የአቤቱታ መዛግብት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እና አቅጣጫ አስቀመጠ።
June 7, 2024
Show all

“እያንዳንዱ ፈፃሚ እና አመራር የሚያስመሰግን ሥራ በመሥራት ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት መሥራት አለበት።” የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ወዬሳ።

ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽ/ቤት አመራሮችና ሠራተኞች ግንቦት 25 እና 26 /2016 ዓ.ም ለ2 ቀናት የዘለቀ ሥልጠና ሱሉልታ በሚገኘው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ተሰጥቷል።

ሥልጠናው የተሰጠው በለውጥ ሥራ አመራር፣ በደምበኞች አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም በሥነ ምግባር መርሆዎች ላይ በዘርፉ ምሁራን ሲሆን በስልጠናው ሁሉም የጽ/ቤቱ አመራሮች እና ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

ስልጠናው የተሰጠው ተቋሙ የተሻለ ሥራ እንዲሠራ  ለማስቻል መሆኑን የገለፁት የአጣሪ ጉባዔ ጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር  አቶ ደሳለኝ ወዬሳ ሁሉንም አካታች ሥልጠና የተሰጠው እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን የተሻለ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ለማስቻል ነው ብለዋል።

በተቋሙ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች መኖራቸውን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ ሁላችንም የለውጥ ሠራዊቶች መሆን አለብን ብለዋል። ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል የሚለውን በዚህ ሥህጠና ራሳችንን ተመልክተናል ያሉት አቶ ደሳለኝ ሁሉም ፈፃሚ እና አመራር ተቋሙን ለመለወጥ በትጋት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ሁላችንም ከራሳችን እንጀምር ያሉት ደግሞ የተቋማዊ ልማት እና  የለውጥ ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተኮላ ወ/ዮሐንስ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት የለውጥ ሥራ ከሳምንታዊ ዕቅድ እና ሪፖርት ባለፈ ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ ነው።  ለተቋሙ ሠራተኞች በአንድነት ስልጠና ከተሰጠ ዓመታት ማለፋቸውን ያወሱት አቶ ተኮላ የዕለቱ ስልጠና በዘርፉ ባለሙያዎች መሰጠቱ የተሻለ ግንዛቤን ለመፍጠር እንደሚያስችልም አክለዋል።

በሌላ በኩል ስልጠናው ከዚህም በላይ እንደየሙያ አይነቶቹ በስፋት መሰጠት አለበት ያሉት ደግሞ የሰው ሀብት ልማት ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት ተወካይ የሆኑት አቶ ሶሪ ቢሼ ናቸው። ከሥልጠና በተጨማሪም የተቋሙን አሠራር ለማሻሻል እና ለማዘመን ለሠራተኞች ማበረታቻ ሽልማቶች፣ የትምህርት ዕድሎች እና ሌሎች ሠራተኞችን የሚያተጉ መፍትሄዎች ተግባራዊ መደረግ አለባቸው ብለዋል።

የተሰጠው ስልጠና ራሳቸውን ለመገምገም፣ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ፣ የረሱትን ለማስታወስ እንዲሁም ሌሎች ብዙ አዳዲስ ዕውቀቶች የተገኙበት መሆኑን ሰልጣኞቹ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለውጥ በአንድ ጀምበር ሳይሆን በሂደት የሚመጣ መሆኑን፣ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ ሥልጠናውም ሰፊ እና ተከታታይነት ባለው መልኩ መሰጠት እንዳለበት፣ እንዲሁም ለውጥ እንዲመጣ ከሥልጠና በተጨማሪ የሠራተኛውን ችግሮች መለዬትና ምላሽ መስጠት እንዲሚያስፈልግ እና ለመለወጥ ከላይኛው አመራር እስከታችኛው ሠራተኛ በተዋረድ መሥራት እንደሚገባ ከሰልጣኞቹ በኩል ተነስቷል።