የሀዘን መግለጫ
June 28, 2019
የዓለም አቀፉ ሕገ መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች ዋና ጸሀፊ ኢትዮጵያን ጎበኙ
July 2, 2019

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕገ መንግስታዊ ፍ/ቤቶችና መሰል ተቋማት ስራ አስፈፃሚ ቢሮ አባል ሆና ተመረጠች

ሕገ መንግስታዊ ፍ/ቤቶች ለሕገ መንግስት፣ ለመሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ዋስትና በሚል ርእሰ ጉዳይ እ.ኤ.አ ከሰኔ 9 እስከ 13 2019 አንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ በተካሄደው 5ኛው የአፍሪካ ሕገ መንግስታዊ ፍ/ቤቶችና መሰል ተቋማት ኮንፈረንስ /conference of constitutional jurisdiction of Africa/ ላይ  ኢትዮጵያ  ከሌሎች ስድስት የአፍሪካ ሀገራት ማለትም ካሜሩን፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ማሊ፣ ሲሸልስና ዙምባብዌ ጋር የስራ አስፈፃሚው ቢሮ አባል በመሆን ተመረጠች፡፡ የአንጎላ ሕገ መንግስታዊ ፍ/ቤት የስራ አስፈፃሚው ፕሬዚዳንት ሲሆን የሞሮኮው ሕገ መንግስታዊ ፍ/ቤት ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡

በስብሰባው ላይ የተገኙትና የኢትዮጵያን ልኡካን ቡድን የመሩት የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ም/ሰብሳቢ አቶ ሰሎሞን አረዳ እንደገለፁት ሀገራችን ኢትዮጵያ የስራ አስፈፃሚ ቢሮ አባል ሆና መመረጧ በአፍሪካና በአለም አቀፍ መድረክ እስከዛሬ ካላት ሚና በተጨማሪ ድርሻዋን አንድ እርምጃ ከፍ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕገ መንግስታችንን ከማስተዋወቅና የሀገራችንን መልካም ገፅታ ከመገንባትም አንፃር ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው በተለያዩ ሀገሮች በየስብሰባዎቹ የሚቀርቡ ፅሁፎችና ውይይቶች የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ እንደተቋም በሕገ መንግስት ትርጉም ዙርያ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም፣ ከአባል ሀገራት ጋር የስራ ትብብር ለመመስረትና ግንኙነትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ ከዚህም  ባሻገር ሀገራችን አሁን ከያዘችው የለውጥና የማሻሻያ እርምጃዎች ጋር በተያያዘ ሕገ መንግስቱን ለማሻሻል ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የልምድና የእውቀት እገዛ ለማግኘት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆንም አቶ ሰሎሞን ጨምረው ጠቁመዋል፡፡

የአንጎላ ሕገ መንግስታዊ ፍ/ቤት 5ኛውን የአፍሪካ ሕገ መንግስታዊ ፍ/ቤቶችና መሰል ተቋማት ስብሰባ ዋቢ አድርጎ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው የአዲስ ተመራጭ የስራ አስፈፃሚዎቹ የስራ ዘመን እ.ኤ.አ ከ2019 – 2021 የሚቆይ ነው፡፡ 6ውን ስብሰባ የምታዘጋጀው ሞሮኮ ስትሆን የስብሰባውን ቀንና ርእሰ ጉዳይ በአፍሪካ ሕገ መንግስታዊ ፍ/ቤቶች ዋና ፀሀፊ የሚወሰን መሆኑን ይኸው መረጃ ያትታል፡፡

በስብሰባው ላይ ሩዋንዳ፣ ሞሮኮ፣ ዚምባብዌ፣ ሶማሊያና ሴራልዮን በአዲስ አባልነት ራሺያና ቱርክ ደግሞ በታዛቢ አባልነት ተመዝግበዋል፡፡ 

ፌስቡክ ገፅ፡- www.facebook.com/CCIFDRE/

ድረ-ገፅ፡- www.cci.gov.et

ኢ-ሜይል፡- constitutionalinquiry.et@gmail.com