ጉባዔው በ100 የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
October 6, 2023
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በአምስት የአቤቱታ መዝገቦች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀመጠ።
October 20, 2023
Show all

አጣሪ ጉባዔው በ122 የትርጉም አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሐሙስ ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ በንዑስ ጉባዔ እና በኤክስፐርቶች ጥናትና ማጣራት ሲደረግባቸው በቆዩ 122 የሕገ መንግሥት የትርጉም አቤቱታዎች ላይ ውሳኔ እና የውሳኔ ሐሳብ ሰጥቷል።

በዕለቱ ለውይይት ከቀረቡት 122 የሕገ መንግሥት ትርጉም የአቤቱታ መዛግብት መካከልም 112ቱ የሕገ መንግሥት ጥሰት አልተፈፀመባቸውም በሚል እንዲዘጉ በጉባዔው ተወስኗል።

በሌላ በኩል 8  የአቤቱታ መዛግብት ላይ በአመልካቾች መልስ እንዲሰጥባቸው በጉባዔው የተወሰነ ሲሆን 1 የአቤቱታ መዝገብ ላይ ደግሞ ተጨማሪ ማጣራት ተደርጎበት ለጉባዔው በድጋሚ እንዲቀርብ ተወስኗል።

ጉባዔው የሕገ መንግሥት ጥሰት ተፈፅሞበታል በሚል በአብላጫ ድምፅ የወሰነው 1 የአቤቱታ መዝገብ ደግሞ በትዳር ፍቺ ወቅት በተደረገ የንብረት ክፍፍል ላይ በስሜ በተመዘገቡ ንብረቶች ላይ የተሰጠን ውሳኔ የመቃወም ጣልቃ ገብ አቤቱታዬ በፍ/ቤቶች ውድቅ በመደረጉ “ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ተጥሷል” በሚል የቀረበ አቤቱታን ይመለከታል።

ፍ/ቤቱ በአመልካች ስም ባለ  ንብረት ላይ ውሳኔ ሲሰጥ አመልካች ወደክርክር እንዲገቡ ጥሪ ባላደረገበት ሁኔታ የመቃወም አቤቱታ ሲያቀርቡ  “ለክርክሩ መነሻ በሆኑት ንብረቶች ላይ መብትና ጥቅም እንዳላቸው እያወቁ የአሁን አመልካች በክርክር ሂደቱ ምስክር ሆነው የቀረቡ በመሆኑ ክርክሩ መካሄዱን ያውቁ ነበር በማለት የመቃወም አቤቱታቸውን ውድቅ አድርጓል፡፡ ሆኖም ግን አመልካች በክርክሩ ውስጥ በከሳሽነት ወይም በተከሳሽነት ወይም በጣልቃ ገብነት ተካፋይ ያልነበሩና ተካፋይ እንዲሆኑም ጥሪ ያልተደረገላቸው በመሆኑ ውሳኔው በአስገዳጅነት በእሳቸው ላይ ሊፈጸም የሚችልበት የሕግ መሠረት የለም የሚል ጭብጥ በጉባዔው ቀርቧል።

አንድ በክርክር ተካፋይ ያልነበረ እና በውሳኔው መብቴ ተጥሷል የሚል መብት ጠያቂ ወደ ክርክሩ ለመግባት በሕግ ያለውን መብት በተመለከተ የፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 358 በግልፅ በደነገገው መሠረት “በክርክሩ ውስጥ ተካፋይ መሆን የሚገባው ወይም በክርክሩ ውስጥ ለመግባት የሚችልና ተካፋይ ባልሆነበት ክርክር የተሰጠው ፍርድ መብቱን የሚነካበት ማንኛውም ሰው ራሱ ወይም ጠበቃው ወይም ነገረ ፈጁ ተካፋይ ባልሆነበት ክርክር የተሰጠው ፍርድ ከመፈጸሙ በፊት መቃወሚያውን ለማቅረብ ይችላል” በማለት በግልፅ ተደንግጓል።

በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠው “ፍትሕ የማግኘት መብት”  ዋነኛ ዓላማ ዜጎች መብታቸውንና ጥቅማቸውን የሚነካ ክርክር ሲደረግ አለኝ ያሉትን ማስረጃ በማቅረብና ክርክር በማድረግ ውሳኔ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህም ተከራካሪ ወገን ሳይሆኑ መብታቸውንና ጥቅማቸውን የሚነካ ውሳኔ ሲሰጥ ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን በመጠቀም የመከራከር መብት አላቸው፡፡ ይህ መብትም በሕግ ከተቀመጠው ስነ ስርዓት ውጭ ሊታጣ አይገባም የሚል ጭብጥ በጉባዔው ተነስቷል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የአሁን አመልካች በአሁን ተጠሪዎች መካከል የተደረገው ክርክር በንብረት መብታቸው ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ በተገነዘቡበት ወቅት የመቃወም አቤቱታ ማቅረባቸውን መዝገቡ ያስረዳል። ፍ/ቤቱ አመልካች በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠላቸውን የመከራከርና ማስረጃ የማቅረብ መብት ሳይጠብቅ በአመልካች ላይ ግዴታ የሚፈጥር ውሳኔ መስጠቱና በክርክሩ ተካፋይ ሳይሆኑ የተሰጠው ውሳኔ እንዲሻርላቸው በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 358 መሠረት ያቀረቡትን አቤቱታ ውድቅ ማድረጉ፤ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን ፍትሕ የማግኘት መብት ይጥሳል፡፡ በሌላ አነጋገር በሕጉ በግልጽ ገደብ ያልተቀመጠለትን መብት ፍ/ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት ገደብ በማበጀት በግልጽ ሕግ የተፈቀደውን መብት የመከልከል ሥልጣን የለውም፡፡ በመሆኑም አመልካች በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 358 መሠረት ያቀረቡት የመቃወም አቤቱታ በፍ/ቤቶቹ ውድቅ  መደረጉ የአመልካችን ፍትህ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚቃረን በመሆኑ ውሳኔው በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 9(1) መሰረት ተፈጻሚነት እንዳይኖረው የሚል የውሳኔ ሐሳብ ለፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላክ ጉባዔው በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።