የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በአምስት የአቤቱታ መዝገቦች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀመጠ።
October 20, 2023
አጣሪ ጉባዔው በ126 የትርጉም አቤቱታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ሰጠ።
October 30, 2023
Show all

አጣሪ ጉባዔው በስኬታማ ሩብ ዓመት አፈፃፀም

የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1፣ ሕገ መንግሥቱ የበላይ ሕግ መሆኑንና ማናቸውም ሕጎች፣ ልማዳዊ አሠራሮችና ውሳኔዎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ ከሆኑ ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው ይደነግጋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 82/1/ መሰረት ተቋቁሞ በአንቀፅ 84/1/መሰረት ለጉባዔው የሚቀርቡትን ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች የማጣራት ስልጣን ያለው ተቋም ነው፡፡ አጣሪ ጉባዔው ማንኛውም ሕግ፣ አዋጅ፣ መመሪያ፣ የመንግሥት አካል ወይም የባለስልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረንና የሚጋጭ ሆኖ ሲያገኘው በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሐሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል፡፡ በሌላ በኩል ለጉባዔው የቀረበለት አቤቱታ የሕገ መንግሥት ትርጉም የማያስፈልገው ነው ብሎ ሲያምን የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ይወስናል፡፡

በዛሬው እትማችንም አጣሪ ጉባዔው የተሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ የሩብ ዓመት አፈፃፀፀሙ ምን ይመስላል ስንል ላነሳነው ጥያቄ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዬሳ  የሰጡትን ምላሽ  ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

አቶ ደሳለኝ ወዬሳ እንደገለፁት፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 82 መሰረት በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ ለጉባዔው የሚቀርቡት አቤቱታዎችም ሆኑ ጥያቄዎች በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ ላይ ከተደነገጉት ድንጋጌዎች አንፃር የተቃኙ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአብዛኛው ለጉባዔው የሚቀርቡ አቤቱታዎች በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የተደነገጉ መብቶቻችን ተጥሰውብናል በሚል የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት  አንቀጾች ተጠቅሰው የሚቀርቡ ቢሆኑም አብዛኞቹ አቤቱታዎች በመደበኛ ፍርድ ቤት ማለቅ የሚገባቸው ክርክሮች እንጅ በእርግጥም የሕገ መንግሥት ጥሰት የተፈፀመባቸው ወይም ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች አይደሉም።

ምንም እንኳን ከባለፉት ዓመታት ጀምሮ የሚቀርቡ የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ጭማሪን ቢያሳዩም አጣሪ ጉባዔው የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ሂደት በከፍተኛ ተነሳሽነት እና ትጋት ውጤታማ  የሚባሉ  ተግባራትን  ማከናወን ችሏል፡፡

አጣሪ ጉባዔው የ2016 በጀት ዓመት እቅዱን የቀመረው በ2015 በጀት ዓመት አፈፃፀም የታዩ ጥንካሬዎችንና ውስንነቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው፡፡ በተለይ ከባለፉት ዓመታት ሲንከባለሉ ቆይተው ወደ አዲሱ በጀት ዓመት ለተላለፉ መዝገቦች ውሳኔ ለመስጠት፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር ለመከወንና ለሕዝቡም የሕገ መንግሥት አስተምሮና የአቤቱታ አቀራረብ  አቅምን ለማጎልበት  ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራበታል።

በዚህም አጣሪ ጉባዔው  በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት   ከሃምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም   504  የአቤቱታ መዛግብት ላይ የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት ‹‹አለ ወይንስ የለም› የሚለውን የማጣራትና የመመርመር ሥራ ሰርቷል፡፡ ከእነዚህ መካከልም 473 በሚሆኑት ላይ  ምንም አይነት የሕገ መንግሥት ጥሰት እንዳልተፈፀመ በማረጋገጥ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልግም የሚል ውሳኔን ሰጥቷል፡፡

አጣሪ ጉባዔው በ10 የአቤቱታ መዛግብት  ላይም የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት ተፈፅሟል በሚል የውሳኔ ሐሳቡን  ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ የመጨረሻ ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሐሳብ ከመሠጠቱ አስቀድሞ በ14 ጉዳዮች ላይ የመሰማት መብትን ለማክበር ተጠሪዎች እና አመልካቾች ቀርበው መልስ እንዲሠጡ  በጉባዔው የተወሰነ ሲሆን 6 የሚሆኑት አቤቱታዎች ላይ ደግሞ ተጨማሪ ምርምርና ጥናቶች ያስፈልጋሉ በሚል በይደር እንዲቆዩ ወስኗል፡፡ ተጠሪዎች መልስ የሰጡበት አንድ ጉዳይ ላይም መሰማት (“public hearing”)  ተደርጓል፡፡

በአጣሪ ጉባዔው ታሪክ በሩብ ዓመት አፈፃፀም  የዘንድሮውን ያህል በቁጥር የበዙ አቤቱታዎች አስፈላጊው ጥናት እና ማጣራት ተደርጎባቸው ውሳኔ ያገኙበት አጋጣሚ የለም፡፡ ይህም ማለት ከዚህ ቀደም በነበረው የአጣሪ ጉባዔው የሥራ አፈፃፀም አቅም በጠቅላላ በጀት ዓመቱ ውስጥ ውሳኔ የሚያገኙ የአቤቱታዎችን ቁጥር በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ ማሳካት ተችሏል። ለዚህ ስኬት ደግሞ የጉባዔ አባላት እና የአጣሪ ጉባዔ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ  ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በሥራ ቀናትም አምሽተው በመሥራት ላስመዘገቡት ስኬት የጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ደሳለኝ ወዬሳ ከፍ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ጉባዔውም መሰል ተግባራትን በመፈፀም በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 9 የተቀመጠውን የሕገ መንግሥት የበላይነት በማስከበር ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ ዜጎች በጉባዔው ላይ እምነት እንዲያሳድሩ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ተግባር መፈፀም ችሏል፡፡

እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻም፣ ይሕ ስኬታማ አፈፃፀምና እምርታ ሊገኝ የቻለው  የአጣሪ ጉባዔው አባላት የላቀ የሥራ ተነሰሽነት፣ የአሠራር ስርዓት አደረጃጀት ለውጦች እንዲሁም ሥራን በዘመቻ የመሥራት ድምር ውጤት ነው፡፡

የባለጉዳዮችን አቤቱታ ከማጣራትና ከመመርመር ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የጉዳዮች አቀራረብና አወሳሰን መመሪያ ተግባራዊ መደረግና የውሳኔ ሐሳብ በሚቀርብባቸው ጉዳዮች ላይ የመሰማት መብትን ለማክበር ተጠሪዎች ቀርበው ሐሳባቸውን የሚያሰሙበት መንገድ መመቻቸቱ  ለተገኘው ውጤት ተጨማሪ አቅም ሆነው ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

እንደ  አቶ ደሳለኝ ገለፃ፤ አንኳር የሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወደ ጉባዔው የመቅረብ ውስንነቶች አሉ፡፡ ለጉባዔው ከሚቀርቡት ጉዳዮች መካከልም የግለሰብ መብትን የሚመለከቱ አብላጫውን ድርሻ የሚወስዱ ናቸው፡፡ የዜጎች ንብረትን የማፍራትና በንብረት የመጠቀም መብት፣ የሴቶችና ሕፃናት መብቶች፣ ከአርሶ አደሮች በእርሻ መሬት የመጠቀምና ከእርሻ መሬት ያለመፈናቀል መብት ጋር የተያያዙም ይገኙበታል፡፡

ለጉባዔው መቅረብ ያለባቸውን ጉዳዮች በመገንዘብ ለይቶ የማቅረብ ችግር በሩብ ዓመቱ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት ካጋጠሙ ችግሮች ዋነኛው ነው፡፡ ከሚቀርቡ አቤቱታዎች መካከል አብዛኞቹም የሕገ መንግሥት ሳይሆን የሕግ ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ሆነው ታይተዋል፡፡

አጣሪ ጉባዔው ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ምላሽ ከመስጠት ባለፈ መሰል ችግሮችን ለማስቀረት በተለይም የሕገ መንግሥት አተረጓጎም ስርዓቱን የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል “የአሠራር ስነ ሥርዓት ደንብ” አርቅቋል፡፡ በደንቡ ላይ ግብዓት ለመሰብሰብም መድረክ በማዘጋጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

የሕገ መንግሥት የበላይነትን ለማስከበር፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎችንና አቤቱታዎችን የማጣራት ሥራን በፍጥነት፣በግልፅነትና ለተገልጋይ ቀላል በሆነ ሁኔታ ለመተግበር፣ ውጤታማነትን ለማሻሻል፣ የጉባዔው አሠራር ወጥነት ያለውና ተገማች እንዲሆን ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡

አጣሪ ጉባዔው በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያት የሕገ መንግሥት ትርጉምም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በማዳበር በኩል ትልቅ ድርሻ በሚኖራቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት ይሠራል፡፡ ከሁለንተናዊ ፋይዳው አንፃር የአሠራር ስነ ሥርዓት ደንቡ ፀድቆ ተግባራዊ እንዲሆን ዘርፈ ብዙ ጥረት ይደረጋል፡፡

በቀጣይም የሕገ መንግሥት የበላይነትን ማስከበር፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎችንና አቤቱታዎችን የማጣራት ሥራን በፍጥነት፣በግልፅነት መከወን፣ በትርፍ ሰዓት በመሥራት ጭምር በተለይም ለዓመታት የተከማቹ  ውዝፍ  አቤቱታዎችን ማቃለል፣ በፍርድ ቤቶችና በአጣሪ ጉባዔው መካከል ያለውን ልዩነት በሚመለከት የሕዝቡን ግንዛቤ ማጎልበት እንዲሁም በአቤቱታ አቀራረብ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ማስተካከል ትኩረት የሚሠጣቸው ዐበይት ተግባራት ናቸው፡፡