የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሁለት የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ላይ ሐሙስ የካቲት 16 ቀን ውይይት በማድረግ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የመጀመሪያው ጉዳይ በባልና ሚስት መካከል የተደረገ የቤት ይገባኛል ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ጉዳዩም የባል እናት በሆነው ይዞታ ላይ የተሠራውን ቤት ሚስት መካፈል አለብኝ በሚል የተደረገን ክርክር ይመለከታል። በጭብጡም ምንም እንኳን ይዞታው የባል እናት ቢሆንም ቤቱን የሠራነው ባልና ሚስት የጋራ ገንዘብ አውጥተን ነው የሚል ነው። በዚህም ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይትና ክርክር ያደረጉት የጉባዔው አባላት በአንድ በኩልከሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እናት ደካማ ከሆኑ በይዞታቸው ላይ ልጆች የሠሩላቸው ቤት በሕግ የንብረት ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል የሚል ሀሳብ ቀርቧል። በሌላ በኩል ይዞታ በሌለበት ቤት የሚባል ነገር ስለማይኖር ቤቱ ከይዞታው ተለይቶ የሚታይበት አግባብ ስለሌለ መሬቱ መወሰዱ በራሱ ሕገ መንግሥታዊ የሚሆንበት አግባብ መኖሩ ተመላክቷል። ጉዳዩም ተጨማሪ ፍሬ ሃሳቦች ተካተውበት ለቀጣይ እንዲቀርብ አቅጣጫ ተሰጥቶበታል።
በመቀጠል ጉባዔው ውይይት ያደረገበት ጉዳይ በጤና ተቋም በማዋለድ ሂደት ውስጥ የወላዷ ሕይወት ስላለፈበት ጉዳይ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ያደረጉት የጉባዔ አባላት ስለ ወላዷ አሟሟት በመጀመሪያ የአስክሬን ምርመራ ተደርጎ ወላዷ በከፍተኛ የህክምና ስህተት የተሠራው የቀዶ ጥገና ስፌት ተፈቶ ብዙ ደም ፈሷት መሞቷ በባለሙያ ተረጋግጦ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በድጋሚ አቤቱታ አቅራቢው ባላወቁበት ሁኔታ ምክንያቱም በውል ሳይገለፅ ውሳኔው ተቀይሮ በሕክምና ሂደት የሚያጋጥም እንጅ የሀኪሙ ስህተት አይደለም መባሉ ግልፅነት የጎደለው ነው በሚል የቀረበ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይም ጉባዔው በስፋት ከተወያየ በኋላ የመጀመሪያውን ውሳኔ መለወጥ የሚያስችል የህግ ድጋፍ መኖር አለመኖሩ? በሁለተኛው ውሳኔ ላይ የተጠሪ የመደመጥ መብት መከልከል አለመከልከሉ? የቅሬታ ሰሚው እና የጤና ሚኒስትሩ ስልጣን ምን ድረስ ነው? እንዲሁም በአሰራር መመሪያው መሰረት ይዘቱን በመተንተን የተሰራ ስህተት መኖር አለመኖሩን ከሕገ መንግሥቱ አንፃር በጥልቀት በመመርመር ለቀጣይ ተጣርቶ ይቅረብ ተብሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ መሰል የሙያ ስህተቶች እየተፈፀሙ ብዙ ሰዎች በተለይም ወላድ እናቶች ጉዳት እንደሚደርስባቸው የገለፁት የጉባዔው አባላት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በግልፅ የጤና ተቋማት ተጠያቂነት፣ የዜጎችም ፍትህ መረጋገጥ አለበት ብለዋል።