አጣሪ ጉባዔው በ 54 የሕገ መንግሥት አቤቱታዎች ላይ ውሳኔ አሳለፈ
February 16, 2023
ከሕገ መንግሥት አተረጓጎም ጋር በተያያዘ የጉባዔውና የፍ/ቤቶች የስልጣን ወሰን ላይ ውይይት ተደረገ።
February 24, 2023
Show all

አዲስ በተሾሙት ሰብሳቢዎች የተመራው አጣሪ ጉባዔሁለተኛ ጉባዔውን አከናወነ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለተኛውን ጉባዔ በማካሄድ 17 የባለጉዳይ አቤቱታዎችን መረመረ።አጣሪ ጉባዔው ትናንት የካቲት 08/2015 ባካሄደው መደበኛ ጉባዔው ቀደም ሲል በዋናና በንዑስ ጉባዔ ደረጃ ውይይት ሲደረግባቸው ከቆዩ ጉዳዮች ውስጥ 17 የባለጉዳይ አቤቱታዎችን መርምሮ 15ቱ ጉዳዮች የሕገ መንግሥት ጥሰት የሌለባቸው ሆኖ ስላገኛቸው ውሳኔ በመስጠት ዘግቷቸዋል።ቀሪዎቹ ሁለት ጉዳዮች በአባላቱ ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ለተጨማሪ ማጣራት እንዲያድሩ ተደርገዋል።ከእነዚህም ጉዳዮች አንዱ በአንድ ግለሰብ መልካችነት ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ጋር ተያይዞ የቀረበ አቤቱታ ሲሆን፣ ጉዳዩም በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ታይቶ የተዘጋ ነው። አመልካችም በኤሌክትሪክ ኃይል አስተላላፊ መስመር ምክንያት የደረሰባቸውን ጉዳት በመጥቀስ፣ በፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገልኝ የአካል ደህንነት መብቴ ተጥሷልና ትርጉም ይሰጥልኝ በማለት ወደ ለአጣሪ ጉባዔው ያቀረቡት ጉዳይ ነው። ጉባዔውም በጉዳዩ ላይ ሰፊ ክርክር ካካሄደ በኋላ የፍ/ቤቶቹ ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊነት ላይ ተጨማሪ ማጣራቶች ተደርገውበት ለሚቀጥለው ጉባዔ ይቅረብ በማለት እንዲያድር ተደርጓል።ሁለተኛው ጉዳይ ከንብረት መብት ጋር ተያይዞ የቀረበ አቤቱታ ሲሆን፣ ተጠሪዎች በውክልና የሰጠኋቸውን ንብረት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ራሳቸው ስም በማዛወርና ቦታውን ሸንሽነው ካርታ በማውጣት ወደ ሌሎች ሰዎች ስላስተላለፉ፣ ይህም በሕገ መንግሥቱ የተደነገገልኝን የንብረት እና ፍትህ የማግኘት መብቴን የሚጥስ ስለሆነ ዝውውሩ ፈርሶ ንብረቴን ከነሙሉ ይዞታው እንዲያስረክቡኝ ለማድረግ የሕገ መንግሥት ትርጉም ይሰጥልኝ በማለት ወደ ጉባዔው የመጣ አቤቱታ ነው።በዚህም ጉዳይ ላይ ጉባዔው በሰፊው ከተወያየ በኋላ አመልካች ለተጠሪ የሰጡት የነበረው ውክልና እስከ ምን ድረስ ነበር? በዚህ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያ ባለንብረቶችና በቅን ልቦና ገዥዎች መብት እንዴት ይታያል? የሚለውና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተጣርተው ለቀጣይ ጉባዔ እንዲቀርቡ በማለት ትዕዛዝ ተሰጥቶ የዕለቱ ጉባዔ ተጠናቋል።