ጉባዔው በ122 የአቤቱታ መዛግብት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ፣ የውሳኔ ሐሳብና አቅጣጫ አስቀመጠ።
January 26, 2024
ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤት ዋና ፀሐፊን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
March 27, 2024
Show all

በጋብቻ ውስጥ ባልና ሚስት የሚያደርጉት የንብረት ስምምነትና ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃው

በጥናትና ምርምር ዳይረክቶሬት ቡድን ሁለት

ውድ አንባብያን ከዚህ በፊት ባቀረብናቸው ጽሑፎች የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት እውቅናና ጥበቃ የሚሰጣቸውን መብቶች አፈጻጸም በጉባዔው እና በፌደሬሽን ምክር ቤት ከተሰጡ ውሳኔዎች አኳያ ይታወቃል፡፡ ዛሬም ባልና ሚስት በጋብቻ ውስጥ የሚያደርጉት ስምምነት ያለውን ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ ይዘት ከዚህ በፊት ከተሰጠው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጋር በማስተሳሰር አዘጋጅተን አቅርበናል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34(2) እና (3) ጋብቻ በተጋቢዎች ነጻና ሙሉ ፈቃድ ላይ ብቻ እንደሚመሰረት የደነገገ ሲሆን በዚህ መሰረት የተመሰረተ ቤተሰብ የሕብረተሰብ የተፈጥሮ መነሻ በመሆኑ ከመንግሥት ጥበቃ እንደሚደረግለት ተደንግጓል፡፡ የተሻሻለው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የቤተሰብ ህግም ለግል ንብረት እውቅና የሚሰጥ ቢሆንም በአንቀጽ 63 መሰረት በአንደኛው ተጋቢ ተመዝግቦ የሚገኝ ማንኛውም ንብረት የጋራ ንብረት እንደሆነ የሕሊና ግምት የሚወስድ ነው፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው አንድን ንብረት ባልና ሚስት የግል ንብረታቸው ለመሆኑ ማስረዳት ካልቻሉ ንብረቱ የጋራ ንብረት እንደሚሆን ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የቤተሰብ ሕጉ ከግል ንብረት ይልቅ ለጋራ ንብረት የበለጠ እውቅናና ጥበቃ የሚሰጥ እና የጋራ ባለሃብትነትን የሚያበረታታ መሆኑ ነው፡፡ ለጋራ ንብረት ቅድሚያ የተሰጠበት ዋና ምክንያት ባልና ሚስት በጋብቻ አብረው በሚኖሩበት ጊዜ ግንኙነታቸው ንብረትን መሰረት ያደረገ እንዳይሆን እና ሕገ መንግሥቱ ለጋብቻ የሰጠውን ልዩ ጥበቃ ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 633(1) እና በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁ. 213/92 አንቀጽ 73 መሰረት ተጋቢዎች በጋብቻ ውስጥ ባሉበት ወቅት የሚያደርጓቸው ውሎች በፍ/ቤት ቀርበው መጽደቅ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡ በጋብቻ ውስጥ ንብረትን አስመልክቶ በባልና ሚስት መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች በፍ/ቤት እንዲጸድቁ የተፈለገበት ዋና አላማ ባልና ሚስት ካላቸው ልዩ የፍቅር ቅንኙነት እና ቀረቤታ በጫና ውስጥ ሆነው ስምምነት እንዳይደረግ ለመከላከል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት ተጋቢዎች በትዳር ውስጥ እያሉ በመካከላቸው የሚያደርጓቸው ውሎች የፍ/ቤት ይሁንታን እንዲያገኙ የተፈለገበት ሌላው ምክንያት ‘ቤተሰብ’ ለሚባለው ተቋም ጥበቃ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በ5ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 6ኛ አመት 2ኛ መደበኛ ስብሰባ በመ/ቁ. 99/13 ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ ያጸደቀው ውሳኔ ባልና ሚስት በጋብቻ ውስጥ ሆነው ያደረጉት ስምምነት በፍ/ቤት አለመጽደቁ ያለውን ሕገ መንግሥታዊ እንደምታ መርምሯል፡፡ የጉዳዩ መነሻ በአመልካች ወ/ሮ ጆቴወርቅ ኪዳኔ እና በተጠሪዎች እነ አቶ ሚልዮን ቅጣው (7 ሰዎች) መካከል በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የተጀመረ የውርስ ንብረት ክርክርን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡

በፍ/ቤቱ በተደረገው ክርክር አመልካች በፍ/ቤት ትእዛዝ ተጣርቶ በቀረበው የውርስ አጣሪ ሪፖርት ላይ ባቀረቡት አስተያየት በአዲስ አበባ ከተማ ቂ/ክ/ከ/ወረዳ 09 የሚገኘው ቤት በ1991 ዓ.ም የባልና ሚስት የጋራ ንብረት እንዲሆን ከሟች ባለቤቴ ጋር ተስማምተን ሟች ቤቱ የጋራ እንዲሆን እና የጋራ ካርታ እንዲሰራልን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ጥያቄ አቅርበው በጋራ ካርታ የተሰራልን ስለሆነ የባልና ሚስት የጋራ ንብረት ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የሟች ወራሾች በበኩላቸው ባቀረቡት አስተያየት አከራካሪው ቤት ሟች አባታችን ከአመልካች ጋር ከመጋባታቸው በፊት በ1975 ዓ.ም ገዝተው ሲኖሩበት የነበረ የግል ንብረት በመሆኑና አመልካች ከሟች ጋር አደረግነው የሚሉት ስምምነትም በፍ/ቤት ባለመጽደቁ ቤቱ የውርስ ንብረት እንጂ የባልና ሚስት ንብረት አይደለም እንዲባልላቸው ተከራክረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠው ፍ/ቤት ባደረገው ማጣራት አከራካሪው ቤት በ2002 ዓ.ም በሟች እና በአመልካች ስም መመዝገቡንና ካርታ የወጣለት መሆኑ አረጋግጧል፡፡ ሆኖም ግን በፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 663(1) እና በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/92 አንቀፅ 73 መሰረት ተጋቢዎች በጋብቻ ውስጥ ባሉበት ጊዜ የሚያደርጉትን ውል በፍ/ቤት ወይም በቤተ ዘመድ ማፀደቅ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡ በአመልካች እና በሟች መካከል የተደረገው የጋብቻ ውል ደግሞ ድንጋጌውን የተከተለ ስላልሆነ ውሉ ህጋዊ ውጤት የለውም ሲል ቤቱ የሟችና የአመልካች የጋራ ንብረት ሳይሆን የሟች የውርስ ሃብት ነው በማለት ወስኗል፡፡    

አመልካችም ውሳኔው ሕገ መንግሥቱን ይጥሳል ሲሉ አቤቱታ አቅርበው በተደረገው ማጣራት በአመልካች እና በሟች መካከል ቤቱን የጋራ ለማድረግ ውል መፈጸሙን እና ውሉ በሟች ሙሉ ፈቃድ የተፈጸመ ስለመሆኑ ከፍ/ቤቱ ውሳኔ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ በዚህም ፍ/ቤቱ በቤተሰብ ሕጉ መሰረት የቀረበለትን ውል መርምሮ ማጽደቅ ወይም አለማጽደቅ እየቻለ ውሉ ተቀባይነት የለውም ሲል መወሰኑ ሕገ መንግሥቱ ለቤተሰብ የሰጠውን ጥበቃ ግምት ውስጥ ያላስገባ እና የአመልካችን ንብረት የማፍራት መብት የሚጥስ ነው ሲል የውሳኔ ሃሳብ ለፌ/ም/ቤት አቅርቦ በሙሉ ድምጽ ተወስኗል፡፡

ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቤት መጀመሪያ የሟች የግል ንብረት የነበረ ቢሆንም ሟች ከአመልካች ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረት በግል ስም የነበረው ካርታ በቤቱ ባለንብረት በነበሩት በሟች ጠያቂነት በባልና ሚስት ስም እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ጉባዔውም በዚህ ደረጃ ስልጣን ባለው የመንግሥት አካል እውቅና የጋራ ካርታ የወጣለትን ቤት፣ በሟችና በአመልካች መካከል የተደረገው ስምምነት የውርስ ክርክሩ ከመጀመሩ በፊት ወይም ሟች እያሉ በፍ/ቤት ቀርቦ አልጸደቀም በሚል ውድቅ ማድረግ የቤተሰብ ሕጉን ከሕገ መንግሥቱ ጋር በሚስማማ አግባብ በመተርጎም አይደለም በሚል ነው፡፡ የቤተሰብ ሕጉም በባልና ሚስት መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች በፍ/ቤት እንዲጸድቁ የፈለገበት ምክንያት ስምምነቱ በጫና ውስጥ የተደረገ እንዳይሆን ለማረጋገጥ ሲሆን ፍ/ቤቱ በየትኛውም የክርክር ሂደት ውሉ ሲቀርብለት መርምሮ የመቀበል ወይም ያለመቀበል ስልጣን አለው፡፡ በዚህ አግባብ የቤተሰብ ሕጉን ከሕገ መንግሥቱ እንዲጣጣም በማድረግ ተፈጻሚነቱን ማረጋገጥ እንደሚቻል ነው፡፡