የጉባዔው የቀድሞ አባላት አዲስ ለተሾሙ የጉባዔ አባላት ልምዳቸውን አካፈሉ
January 21, 2022
ጉባዔው በ26 የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
April 16, 2022

በአዲስ አባላት የተዋቀረው ጉባዔ የመጀመሪያ ውይይቱን አደረገ

ከመንግሥት ምስረታ በኋላ አዲስ የተሾሙት የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላት የተገኙበት የመጀመሪያው ጉባዔ የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ፍ/ቤት አዳራሽ በሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ተካሄደ፡፡

ውይይቱን የመሩት የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ አዳዲስ አባላትን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ትውውቅ ካደረጉ በኋላ ቀደም ሲል የነበረውን የጉባዔ አሰራር ለአባላቱ አጋርተው አዳዲስ የጉባዔ አባላትም ያላቸውን አጠቃላይ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ጋብዘዋል፡፡

በጉባዔው አባላት ከተነሱት ጉዳዮች መካከል በተለይ የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በሚባሉ ጉዳዮች ላይ የመሰማት መብትን ለማክበር ተጠሪዎች ቀርበው ሀሳባቸውን የሚያሰሙበት መንገድ /Hearing/ ቢመቻች፣ አብዛኛው ጉዳይ ከፍ/ቤት የሚመጣ ከመሆኑ አንፃር ጉባዔው ከሰበር ሰሚ ፍ/ቤቱ ጋር የሚናበብበት መንገድ ቢመቻች፣ የውሳኔ ጥራት እንዲኖርና የሕዝብ አመኔታ እንዲጨምር አወያይና ህዝብን የሚያስተምሩ ጉዳዮች ላይ መድረክ አመቻችቶ መወያየት ቢቻል የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ክብርት ሰብሳቢዋም የመሰማት መብትን በተመለከተ ቀደም ሲልም ሲነሳ የነበረ እንደነበረ ጠቁመው ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ማድረግ እንደሚቻልና ለዚህም የአሰራር ስርዓት ማስቀመጥ እንደሚያስፈልገው ገልፀዋል፡፡ አወያይና አስተማሪ የሆኑ ጉዳዮችን በተመለከተ የጉዳዩ አይነት ተለይቶ ጥናት እንዲደረግበት በጉባዔው ከፀደቀ በኋላ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሙያዊ ሀሳብ እንዲቀርብ በማድረግ መድረክ አመቻችቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረግ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

ወደ መደበኛው አጀንዳ ሲመለስ ጉባዔው ሶስት ጉዳዮችን የተመለከተ ሲሆን በጉዳዮቹ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ሁለቱ ጉዳዮች ተጨማሪ ማጣራት ተደርጎባቸው በድጋሚ እንዲቀርቡ፣ ቀሪውና የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል የተባለ አንድ ጉዳይ ላይ ቀደም ሲል ጉባዔው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተጠሪን የመስማት ፕሮግራም ለማካሄድ በፅ/ቤቱ በኩል ቀጠሮ እንዲያዝ በመወሰን የእለቱን ውይይት አጠናቋል፡፡