ጉባዔው በ7 የአቤቱታ መዛግብት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እና አቅጣጫ አስቀመጠ።
June 7, 2024
ጉባዔው በ80 የአቤቱታ መዛግብት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እና አቅጣጫ አስቀመጠ።
June 18, 2024
Show all

በሩስያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የብሪክስ አባል ሀገራት የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንቶች ጉባዔ ኢትዮጵያ በክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በመወከል እየተሳተፈች ትገኛለች።

ከሰኔ 10 እስከ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም በሩስያ ሶቺ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የብሪክስ አባል ሀገራት የጠቅላይ ፍ/ቤ ፕሬዝዳንቶች የጋራ ጉባዔ ሀገራችን ኢትዮጵያን በመወከል የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ በሆኑት በክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የተመራ ልኡክ በመድረኩ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። በዚሁ መድረክ ላይ ከአስተናጋጇ ሩስያ እና ከሀገራችን ኢትዮጵያ በተጨማሪ፤ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ የቻይና፣ የሕህንድ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የግብፅ፣ የኢራን እንዲሁም የቤላሩስ ጠቅላይ ፍ/ቤቶ ፕሬዝዳንቶች ተሳታፊዎች መሆናቸው ተመላክቷል።

በዛሬው ዕለት በነበረው የጧት መርሃ ግብር ላይ የኢዴፌሪ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ከሩስያ ፌዴሬሽን አቻቸው ኢሪና ፖድኖሶቫ እንዲሁም ከሌሎች የሩስያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ የተሳካ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

በውይይቱም ሁለቱ ሀገራት ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው በማውሳት፤ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሠሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በዚህም በሁለቱ ሀገራት ፍ/ቤቶች መካከል ያለውን ትስስር አጠናክሮ ለመቀጠል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን በዘርፉ ላይም በትምህርት፣ በአጫጭር ስልጠናዎች፣ በአይሲቲ እና በቴክኖሎጂዎች በአጠቃላይ በአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በጋራ ለመሥራት ሰፊ ውይይት በማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል።

በሩሲያ ሶቺ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የብሪክስ አባል ሀገራቱ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንቶች ጉባዔ እስከ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቀጥል ሲሆን  በዛሬው መርሃ ግብር የሩሲያው ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ከኢትዮጵያ አቻቸው ከክቡር አቶ ቴዎድሮስ በተጨማሪ ከግብፅ፣ ከቻይና እና ከቤላሩስ አቻዎቻቸው ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ከየተያዘው ፕሮግራም ለመረዳት ተችሏል፡፡

በነገው እለትም በክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የሚቀርበውን የብሪክስ አባል ሀገራት የወጡ ሕጎችን የማቀራረብ ወይም የማስማማት ሂደት የተመለከተውን ርዕሰ ጉዳይ ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር እንደሚደረግ ከተያዘው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።