ለጋብቻ የሚደረግ ጥበቃ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት
December 21, 2022
ለጋብቻ የሚደረግ ጥበቃ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት
January 4, 2023

በሀይማኖታዊ ወይም በባህላዊ ተቋማት የመዳኘት መብት ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንጻር

በጌታቸው ጉዲና

ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት እንዳለው በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 37 ንኡስ አንቀጽ 1 በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህ መብት ክስ እና ማስረጃን፣ መልስና መከላከያን የማቅረብ፣ ምስክሮችን የመጠየቅ፤ የመከራከር፣ የመሰማት፣ በጠበቃ የመወከል፣ በተቻለ መጠን አፋጣኝ ውሳኔ የማግኘት፣ በተሰጠው ውሳኔ ቅር በተሰኙ ጊዜ ሥልጣን ላለው ፍ/ቤት ይግባኝ የመጠየቅና ወዘተ… የሚያጠቃልል ይሆናል፡፡

በፍርድ ሊታይ የሚችልን ጉዳይ አይቶና አከራክሮ ውሳኔ መስጠት የሚችለው መደበኛ ፍ/ቤት ቢሆንም በልዩ ሁኔታ እና ሕግ በሚፈቅደው አግባብ እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ከመደበኛ ፍ/ቤት ውጪ የሚታዩበት አግባብ ሊኖር ይችላል ማለት ነው፡፡ በዚህ ሕገ መንግስት ድንጋጌ መሰረት ከፍ/ቤት (ከመደበኛ ፍ/ቤት) ውጭ በፍርድ ሊወሰን የሚገባን ጉዳይ ሊያይ የሚችል በሕግ ሥልጣን የሚሰጥ አካል ሊኖር እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 78(4) የዳኝነት ሥልጣንን ከመደበኛ ፍ/ቤቶች ወይም በሕግ የመዳኘት ሥልጣን ከተሰጠው ተቋም ውጭ የሚደረግ፤ በሕግ የተደነገገን የዳኝነት ሥርዓት የማይከተል ልዩ ፍ/ቤት ወይም ጊዜያዊ ፍ/ቤት አይቋቋምም በማለት ይደነግጋል፡፡ ይህ ድንጋጌ የሚያስረዳው ማንኛውም መደበኛ ፍ/ቤትም ሆነ በሕግ የመዳኘት ሥልጣን የተሰጠው አካል መከተል የሚችለው (የሚገባው) ሥነ ሥርዓት መደበኛ ፍ/ቤቶች ከሚከተሉት ሥነ ሥርዓት ወጭ መሆን እንደማይችልና እንደዚህ አይነት ተቋም ሊኖር እንደማይችል ወይም በሕግ ሊቋቋም እንደማይችል ነው፡፡

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 34(5) መሰረት ሕገ መንግሥቱ የግል እና የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ በተከራካሪዎች ፈቃድ በኃይማኖቶች ወይም በባህል ሕጎች መሰረት መዳኘትን እንደማይከለክል እና ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰን በግልፅ ተደንግጓል፡፡ በሀይማኖታዊም ሆነ በባህላዊ ተቋማቶች ዜጎች የግልም ሆነ የቤተሰብ ጉዳይቸውን ሲያቀርቡ መሟላት የሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

በዚህ ጉዳይ ሶስት ዋና ዋና ነጥቦችን እንመለከታለን፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ ሀይማኖታዊ ወይም ባሕላዊ ተቋማቱ ጉዳዩን ለማየት በሕግ ሥልጣን ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መደበኛ ፍ/ቤቶችም ሆኑ ሌሎች በሕግ የመዳኘት ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት አንድን ጉዳይ ተቀብለው ከማስተናገዳቸው በፊት ጉዳዩን አይተው የመወሰን ስልጣን እንዳላቸው የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡ አንድን የዳኝነት ጉዳይ አይቶ ውሳኔ ለመስጠት ሥልጣን የሚሰጠው ግልጽ ሕግ ሳይኖር ጉዳዩን ተቀብሎ ማስተናገዱ የሕገ መንግስት ጥያቄ ከሚያስነሱ መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡  

ሁለተኛው ነጥብ ጉዳያቸው በሀይማኖታዊ ወይም በባሕላዊ ተቋማቱ የሚታይላቸው ግለሰቦች ሙሉ ፍቃደኝነት ሊኖር ይገባል፡፡ ከላይ ከሕገ መንግስቱ ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው አንድ ግለሰብ ጉዳዩ በሀይማኖታዊ ወይም በባሕላዊ ተቋማት ሊዳኝ የሚችለው ባለጉዳዩ (ሕጋዊ ወኪሉ) በነዚህ ተቋማት ለመዳኘት ያለምንም ተጽእኖ በሙሉ ፍላጎቱ ፈቅዶ የቀረበ መሆን አለበት፡፡ ተቋማቱም የግለሰቡ ፍቃደኝነት መኖሩን በማያሻማና ለትርጉም በማያጋልጥ መልኩ ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡  

ሦስተኛው ነጥብ በሀይማኖታዊ ወይም በባሕላዊ ተቋማቱ ላይ ሊታይ የቀረበው ጉዳይ የግል ወይም የቤተሰብ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ማሕበራዊ ነክ ጉዳዮች በሀይማኖታዊ ወይም በባሕላዊ ተቋማት ሊዳኙ እንደሚችሉ በሕገ መንግስቱ እውቅና አልተሰጠም ማለት ነው፡፡ በሀይማኖታዊ ወይም በባሕላዊ ተቋማት በፍርድ ሊዳኝ የሚችል ጉዳይ ለመቅረብ እነዚህ ሶስቱ ቅደመ ሁኔታዎች በአንድነት የተሟሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ጉዳዮች ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ቀርቦ ውሳኔ እና የውሳኔ ሀሳብ የተሰጠባቸው ሲሆን ከተከራካሪ ወገኖች ፍቃድ ጋር ተያይዞ በሀይማኖታዊ ፍ/ቤት የተሰጠው ውሳኔን አስመልክቶ የቀረበለት ጉዳይ ላይ ጉባኤው መርምሮ በመዝገብ ቁጥር 1352/07 በግንቦት 06 ቀን 2007 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የሕገ መንግሥት ጥሰት አለበት በማለት ለፌዴሬሽን ም/ቤት የውሳኔ ሀሳብ የላከበትን እንደማጣቀሻ ማንሳት ይቻላል፡፡

የጉዳዩ ይዘትም ባጭሩ አመልካች ከተጠሪ ጋር በጋብቻ አብሮ ሲኖሩ ቆይተው ተጠሪ አመልካችን ለእረፍት ወደ አሜሪካን ሀገር ከላኩ በኋላ በ16/03/06 ለፌዴራል የመጀመሪያ ፍ/ቤት የፍቺ አቤቱታቸውን በማስገባት በቀን 20/03/06 ዓ.ም (ከአራት ቀን በኋላ) በታተመው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለቀን 02/04/06 እንዲቀርቡ የጥሪ ማስታወቂያ አሰወጥተዋል፡፡ ፍ/ቤቱም አመልካች በሌሉበት በቀን 10/04/2006 የፍቺ ውሳኔ ስለሰጠ አመልካች በሸሪአ ፍ/ቤት ለመዳኘት በግልጽ ሀሳቤን ሳልሰጥ የተሰጠው ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 34(5) እንዲሁም የፌዴራል ሸሪአ ፍ/ቤቶችን አቋም ለማጠናከር በወጣው አዋጅ ቁጥር 188/92 አንቀጽ 5(2) መሰረት በቅድሚያ መጥሪያ በአግባቡ እንደደረሰኝ ማረጋገጥ ሲገባው አላረጋገጠም፡፡ በዚሁም ምክንያት ፍ/ቤቱ ሥልጣን ሳይኖረው ጉዳዬን አይቶ ውሳኔ ሰጥቷል የሚል አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

አጣሪ ጉባኤውም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ በደረሰው መደምደሚያ አመልካች ውጭ ሀገር መኖራቸውን ተጠሪ እያወቁ፣ ፍ/ቤቱም መጥሪያ እንዲደርሳቸው በቂ ጊዜ መስጠት ሲገባው የፍቺ ጥያቄ ለሸሪአ ፍ/ቤቱ በ16/03/06 ቀርቦ የጥሪ ማስታወቂያ በ20/03/06 በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲወጣ በማድረግ አመልካች ፍቃድ መስጠታቸውን ሳያረጋግጥ የሰጠው የፍቺ ውሳኔ የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 34(5) ይቃረናል በማለት የውሳኔ ሀሳቡን ለፌ/ም/ቤት ልኮ ም/ቤቱም የውሳኔ ሀሳቡን ተቀብሎ በመ.ቁ. 08/09 በቀን 03/07/2008 በ5ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 1ኛ አመት 2ኛ መደበኛ ስብሰባ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡  

በአጠቃላይ በሀይማኖታዊ ወይም በባሕላዊ ተቋማት በፍርድ ሊዳኝ የሚችልን ጉዳይ ለመመልከትና ለመወሰን በፍርድ ወይም በውሳኔ ሂደታቸው በሕገ መንግሥቱ የተመለከቱትን የግለሰቦቹን መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶችን ባከበረ መልኩ ማየትን ይጠይቃል፡፡