የፕሬስ መግለጫ የህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ
May 12, 2020
“አሁን ያለንበትን ወቅት የሕገ መንግሥት ጊዜ በማለት ልንጠራው እንችላለን” ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ
May 20, 2020

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሚመለከት በቀረበ የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ሂደት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

????????????????????????????????????

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሚመለከት በቀረበ የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ሂደት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ከኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በተላከው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚመለከት የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ሂደት ላይ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም በጠቅላይ ፍ/ቤት አዳራሽ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ፡፡

የጉባኤው ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ መአዛ በመግለጫው ላይ እንደገለፁት ጉዳዩ ክብደት ያለው ሀገራዊ ጉዳይ በመሆኑ ጥያቄው ከመጣበት ከሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከተለመደው አካሄድ በመውጣት በልዩ ሁኔታ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ጉባኤው የራሱን የመወያያ ጭብጥ ይዞ እየተወያየ እንዳለ ጠቅሰው ጭብጦቹን መሰረት ያደረገ ጥናት በውስጥ ባለሙያዎች እያስጠና እንዳለና ከውጭም ከፍተኛ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ፅሁፍ እንዲቀርብ ጥሪ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በቀጣይም ፅሁፍ የሚያቀርቡ ባለሙያዎች ተለይተው የፍርድ ቤት ስርአትን በመከተል የፊታችን ቅዳሜና ሰኞ ሀሳቦች ቀርበው የሚደመጡበት ጊዜ እንደሚሆን ጠቁመው በመጨረሻም በመድረክ የተነሱ ሀሳቦችንና የተለያዩ ፅሁፎችን መሰረት አድርጎ ጉባኤው ውይይት በማድረግ ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሀሳብ እንደሚያስተላልፍ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም ከጋዜጠኖች የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን ከውሳኔ ገለልተኝነት እና ጉዳዩን ከማየት ስልጣን ጋር፣ የብዙዎችን አስተያየት ማሳተፍ ከሚፈጥረው ወገንተኝነት አንፃር እንዲሁም ከፅሁፍና ከመድረክ ተሳታፊዎች ተሳትፎ አግባብ ጋር ተያይዞ የተነሱት ዋናዋናዎቹ ናቸው፡፡

ሰብሳቢዋ ለጥያቄዎቹ መልስ ሲሰጡ ጉባኤው በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 83 እን 84 መሰረት ጉዳዩን የማየት ስልጣን እንዳለው፣ ገለልተኝነትን በተመለከተ ጉባኤው እስካሁን ነፃ በሆነ መንፈስ ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮችን የሚያይበት አሰራር በመኖሩ አሁንም በዚያው መንፈስ እየሄደ እንደሆነ፣ የፅሁፍ አቅራቢዎችን በተመለከተ የአቀራረብ መመሪያ ወጥቶለት በመስፈርቱ መሰረት የሚከናወን መሆኑን፣ የተለያዩ ሀሳቦችን ማሳተፍና ማዳመጥ ለውይይቱ መበልፀግ ድርሻ ይኖረዋል እንጂ ሀሳቦች መቅረባቸው በራሱ አሳሳቢ እንዳልሆነ ጠቁመው ብዙ ሀሳቦች  ቀርበው ውይይት የሚደረግበት በመሆኑ እንደውም ጊዜው “የሕገ መንግስት መልካም ጊዜ” ሊባል የሚችልበት ጊዜ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡