ጉባዔው በ12 የአቤቱታ መዝገቦች ተወያይቶ ሶስቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም ሲል እንዲዘጉ ወሰነ።
April 18, 2023
ጉባዔው ከቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ላይ የመስማት /Public Hearing/ ስነ ሥርዓት አካሄደ
May 1, 2023

ማንኛውም ሰው የፈፀመው ድርጊት በወንጀል ሕግ ጥፋት መሆኑ ካልተደነገገ በስተቀር አይቀጣም !

ከጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት

ውድ አንባብያን ከዚህ በፊት ባቀረብናቸው የሕገ መንግስት ትርጉም ትንተናዎች ጠቃሚ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እናምናለን፡፡ ዛሬም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት ጥበቃና እውቅና ከሰጣቸው መብቶች መካከል በወንጀል ሕግ ጥፋት ባልተሰኘ ተግባር ያለመቀጣት መብት አጣሪ ጉባኤውና የፌዴሬሽን  ምክር ቤት ከዚህ በፊት ከሰጡት ውሳኔ አንጻር ያለውን ትንተና ነው፡፡

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 22(1) መሠረት ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ሲቀርብበት የተከሰሰበት ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ ድርጊቱ ወንጀል መሆኑ በሕግ የተደነገገ ካልሆነ በስተቀር ሊቀጣ አይችልም በማለት ደንግጓል፡፡ ከዚህም ለመረዳት የምንችለው ማንኛውም ሰው በወንጀል ተከሶ ሊቀጣ የሚችለው ድርጊቱ በሚፈጸምበት ወቅት ለክሱ መነሻ የሆነው ድርጊት በወንጀል ሕጉ እንደ ጥፋት የሚቆጠር ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ተፈጸመ የተባለው ድርጊት በወንጀል ሕጉ እንደ ጥፋት ተቆጥሮ ሕግ ያልወጣለት ከሆነ በድርጊቱ ምክንያት ቅጣት ማስተላለፍ አይቻልም ማለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቴክኖሎጂ በፍጥነት በመለዋወጡ፣ መንግስት በአንድ ጉዳይ ላይ የፖሊሲ ለውጥ በማምጣቱ ወይም በሌላ ምክንያት እንደ ወንጀል ሲቆጠሩ ያልነበሩ ድርጊቶች በሂደት ከሕገ መንግስቱ በተጣጣመ አግባብ ወንጀል ሕጉን በማሻሻል የወንጀል ጥፋት ተደርገው ሊቆጠሩ ቢችሉም ሕጉ ከመሻሻሉ በፊት የተፈጸሙ ድርጊቶች ግን በወንጀል ሊያስጠይቁ አይችሉም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 22(2) ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ወይም ለተቀጣው ሰው ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ ከድርጊቱ በኋላ የወጣው ሕግ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ተደንግጓል፡፡ የወንጀል ቅጣት ዋና አላማ ጥፋተኛውን በማስተማር የተሻለ ዜጋ መፍጠር ነው፡፡ ለዚህም የወንጀል ቅጣት የሚፈጸምባቸው ተቋማት ዋና ተግባርና ሃላፊነት በቁጥጥራቸው ስር የሚገኙ የወንጀል ቅጣት የተጣለባቸውን ዜጎች የማስተማርና የማነጽ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግስቱ የወንጀል ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የወጣው ሕግ ለተከሳሹ የሚጠቅም ሆኖ ከተገኝ ተከሳሹን በአዲሱ ሕግ የመዳኘት መብትን ያጎናጽፈዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ከዚህ በፊት የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 22 አፈጻጸምን አስመልክቶ በርካታ ውሳኔ ሃሳቦች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ የመጨረሻ ውሳኔ አግኝተዋል፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ለዛሬው እትም ጉባዔው የውሳኔ ሃሳብ ካቀረበባቸውና በምክር ቤቱ ውሳኔ ካገኙ ጉዮዮች አንዱን አቅርበናል፡፡

ጉዳዩ ነሐሴ 5 ቀን 2008 ዓ.ም በአቶ ንጉሴ ሀድጎ እና በኦሮሚያ ክልል ዐቃቢ ሕግ የተደረገውን ክርክር ይመለከታል፡፡ ዐቃቢ ሕግ ለፍ/ቤቱ ባቀረበው ክስ ተከሳሽ የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 32(1ሀ) እና የንግድ ፍቃድ አዋጅ ቁ. 686/2002 አንቀጽ 6(4) እና 60(3) በመተላለፍ በዳሌ ወበራ ወረዳ ቂጮ መንደር ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ለወረዳው ንግድ ጽ/ቤት ሳያሳውቅ 169 ኩንታል ሚጥሚጣ ገዝቶ ጭኖ ሊወጣ ተይዟል በማለት ለሚመለከተው አካል ሳያሳውቅ ቅርንጫፍ በመክፈት የንግድ ስራ ላይ የመሰማራት ወንጀል ፈጽሟል ሲል ክስ መስርቷል፡፡ ተከሳሽም የጸና ንግድ ፈቃድ ያላቸው መሆኑ ጠቅሰው ሽያጭ እስካልፈጸምኩ ድረስ  ግዢውን ለመፈጸም ቅርንጫፍ የመክፈት ግዴታ የለብኝም በማለት ክሱ ውድቅ እንዲደረግላቸው ክርክር አቅርበዋል፡፡

ጉዳዩን በመጨረሻ የተመለከተው ፍ/ቤት ተከሳሽ የጸና ንግድ ፈቃድ ያላቸው መሆኑ ቢረጋገጥም በአንድ ክልል ያወጡት ንግድ ፈቃድ በመጠቀም በሌላ ክልል ግዥ ለመፈጸም የማሳወቅ ግዴታ ነበረባቸው ሲል ጥፋተኛ ናቸው በማለት ሚጥሚጣው የወንጀል ፍሬ በመሆኑ እንዲወረስ እና ተከሳሽም በንግድ ምዝገባ አዋጅ ቁ. 686/2002 አንቀጽ 6(4) መሠረት በሶስት ዓመት ጽኑ እስራትና በብር 30,000 (ሰላሳ ሺ) የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ አመልካችም ለጉባኤው ባቀረቡት አቤቱታ በእጄ ላይ የንግድ ፈቃድ እያለ ከሌላ ክልል በርበሬ ለመግዛት አላሳወቅም በሚል በወንጀል መቀጣቴ በሕገ መንግስቱ ከተረጋገጠው ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ  የመስራት መብት ጋር ይቃረናል በማለት በውሳኔው ላይ የሕገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡

ጉባኤውም ባደረገው ማጣራት አመልካች ጥፋተኛ የተባሉበት የንግድ ምዘገባ አዋጅ ቁ. 686/2002 አንቀጽ 6(4) በብዙ ስፍራዎች ቅርንጫፍ የሚከፍት ሰው አግባብነት ያለውን ማመልከቻ ቅጽ በመሙላት የንግድ ምዝገባ ምስክር ወረቀትና የንግድ ፈቃድ ፎቶ ኮፒ በማያያዝ ማቅረብ እንዳለበት ይደነግጋገል፡፡ ሆኖም ግን አመልካች ስልጣን ባለው አካል የተሰጠ የበርበሬ ጅምላ ንግድ ፈቃድ ያላቸው ሰለመሆኑ አካራካሪ አልነበረም፡፡ አመልካችም በተሰጣቸው ንግድ ፈቃድ መሠረት በርበሬ ከመግዛት ውጪ በመሸጥ በመለወጥ ተግባር ያልተሰማሩ በመሆኑ ቅርንጫፍ የመክፈት ግዴታ የለባቸውም፡፡

የመንግስቱ አንቀጽ 32 ማንኛውም ሰው ተዘዋውሮ የመስራት መብትን ያረጋገጠ ሲሆን የሕገ መንግስቱ አላማም አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ መፍጠር ነው፡፡ ስለሆነም አመልካች ጸንቶ ባለው ንግድ ፈቃድ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል በመሄድ የበርበሬ ግዥ ማድረጋቸው በግልጽ የወንጀል ድርጊት ነው ተብሎ በአዋጁ አልተደነገገም፡፡ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 22(1) መሠረት አንድ ድርጊት በወንጀል ሊያስቀጣ የሚችለው ድርጊቱ በሚፈጸምበት ጊዜ በሕግ የሚያስቀጣ መሆኑ ሲደነገግ ነው፡፡ ሆኖም ግን የአመልካች ድርጊት ግዥ መፈጸም ሲሆን በአዋጁ የወንጀል ድርጊት ስለመሆኑ ያልተደነገገ በመሆኑ ፍ/ቤቱ ያስተላለፈው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ሕገ መንግስቱን ይጥሳል በማለት ጉባኤው የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱም የጉባኤው የውሳኔ ሃሳብ ከመረመረ በኋላ ውሳኔ ሃሳቡን በመቀበል የፍ/ቤቱ ውሳኔ በመሻር ወስኗል፡፡

የውሳኔው እንደምታ ስንመለከት ማንኛውም ነጋዴ በአንድ ክልል ያወጣው ንግድ ፈቃድ በመጠቀም በሌላ ክልል ግዥ መፈጸም እንደ ወንጀል ድርጊት ሊቆጠር እንደማይገባ ነው፡፡ ሆኖም ግን ነጋዴው የገዛውን እቃ ለመሸጥ ለመወጥ ሲፈልግ አሁንም በድጋሚ ንግድ ፈቃድ ማውጣት ሳያስፈልገው ለሚመለከተው ክልል በማሳወቅ ቅርንጫፍ የመክፈት ግዴታ ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም ውሳኔው ዜጎች በአገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ የሚገድቡ አሰራሮችና ውሳኔዎችን በማረም አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ለመፍጠር መንገድ የሚከፍት ነው፡፡