የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ለመላው ኢትዮጵያውያን  እንኳን ለአዲሱ አመት በሰላም አደረሳችሁ እያለ ፡ 2013 ዓ.ም የሰላም የፍቅር እና የብልጽግና ዘመን እንዲሆንላችሁ ይመኛል
September 8, 2020
ጉባዔው በሦስት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሀሳብ አሳለፈ
October 22, 2020

ሕገ መንግሥቱን በትርጉም ማዳበር ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማዳበር እንደሚረዳ ተገለፀ

ሕገ መንግሥቱን በትርጉም ማዳበር ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማዳበር እንደሚረዳ ተገለፀ

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በ2012 በጀት ዓመት በጉባዔው ታሪክ የተለየ የሚባልና  ሕገ መንግሥቱን ከማዳበር አንጻር ትልቅ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች በጥልቀት የመረመረበት ጊዜ መሆኑን የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ እና የጠቅላይ ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ሰሎሞን አረዳ ገለፁ ፡፡

ጉባዔው በበጀት ዓመቱ ከጣራቸውና በተለይም የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ብሎ ለመጨረሻ ውሳኔ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳቡን ካሳለፈባቸው 10 ጉዳዮች መካከል ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ምርጫን በወቅቱ ማካሄድ ባለመቻሉ እንዲሁም የምክር ቤቶችንና የአስፈጻሚ አካላትን የሥራ ዘመን አስመልክቶ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ዋነኛውና ተጠቃሹ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ጉባዔው ከተለያዩ  አቅጣጫዎች አንጻር በመመርመርና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የተለያዩ የሕግ ባለሙያዎችና ተቋማትን አሳትፎ አስተያየታቸውን በማዳመጥ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ስርጭት በሚዲያ እየተላለፈ ለህዝብ ይፋ በሆነ መድረክ በቀጣይ ሕገ መንግሥታዊ የትርጉም ሥርዓትን ሊያሰፉ የሚችሉ አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትንተና በመስጠት የውሳኔ ሀሳብ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ይህ ሂደት በሀገራችን የሕገ መንግሥት ታሪክ እንደ ትልቅ አዲስ ምዕራፍ ሊታይ የሚችል መሆኑ ላይ አጽንዖት የሰጡት ምክትል ሰብሳቢው ባደጉ ሀገራት የሕገ መንግሥት ትርጉም ላይ የሚደረጉ ክርክሮችና የሚሰጡ ውሳኔዎች ሕገ መንግሥትን የማዳበርና ከትውልድ ትውልድ የሚሻገር ሰነድ የማድረግ ሚና ያላቸው እንደሆነ ጠቅሰው፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማዳበር ከሚረዱ ዐበይት ተግባራት መካከል ሕገ መንግሥቱን በትርጉም ማዳበር ዋነኛው እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ምክትል ሰብሳቢው እንደገለፁት አሁን ሀገራችን ካለችበት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ አንጻር ለሕገ መንግሥቱ መዳበር ሚና የሚኖራቸው የሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ጥያቄዎች የማቅረብ ፍላጎት እየጨመረ ስለሚሄድ ጉባዔው አንኳር አንኳር ከሆኑ ዐበይት ክስተቶች ጋር ተያይዞ በሚነሱ አለመግባባቶች፣ አሊያም በተለያዩ የመንግሥት የስልጣን መዋቅር መካከል በሚደረጉ የሥራ ግንኙነቶች የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎች ቢቀርቡለት ካለፉት ጊዜያት በተወሰዱ ልምዶች የበለጠ በተጠናከረ መልኩ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችለው ደረጃ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በጉባዔው የጸደቀውና በያዝነው በጀት ዓመት ተግባራዊ የሚደረገው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የጉዳዮች አቀራረብና አወሳሰን መመሪያ ጉባዔው ተራ የመደበኛ ፍርድ ቤት ጉዳዮችን ከማየት ሕገ መንግሥታዊ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮችን ወደ መመርመር የማሻገር ሚና እንዲኖረው የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡